ሱዳን መንግስትን እና ህወሓትን ለማደራደር ታዓማኒነት እንደሚጎድላት መንግስት አስታወቀ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሱዳን መንግስትንና ህወሃትን ለማሸማገል እንቅስቃሴ ስለመጀመሯ የማውቀው ነገር የለም ብሏል
ሱዳን ለማሸማገል ከማሰቧ በፊት ማስተካከል የሚጠበቅባት ብዙ የቤት ስራዎች እንዳሉም ተገልጿል
ሱዳን የኢትዮጵያ መንግሥትን እና ህወሓትን ለማሸማገል ከማሰቧ በፊት ጦሯን ከኢትዮጵያ ማስወጣት እና መታመን እንዳለባት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታወቀ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ቢለኔ ስዩም ሱዳን መንግሥትን እና ህወሓትን የማሸማገል ሃሳብ እንዳላት ተጠይቀው ሱዳን በዚህ ወቅት ለማደራደር ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የሆነውን ታዓማኒነት እንደማታሟላ አስታውቀዋል።
አሁን ላይ የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ መሆኑን የጠቀሱት የፕሬስ ሴክሬታሪዋ የሱዳን ባለስልጣናት የካርቱም እና የአዲስ አበባ ግንኙነት እንዲሻክር ባደረጉበት በዚህ ወቅት ሱዳን ታማኝ አደራዳሪ ልትሆን እንደማትችል ገልጸዋል።
በመሆኑም ለማደራደር በቅድሚያ እነዚህ ነገሮች መፈታት እና መስተካከል እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም አስታውቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ዛሬ ጠዋት በሰጡት መግለጫ ሱዳን የኢትዮጵያ መንግስትን እና ህወሃትን ለማነጋገር እና ለማሸማገል እንቅስቃሴ መጀመሯ ስለመገለጹ እንደማያውቁ ገልጸዋው “እኛ ገና ከሱዳን ጋር ብዙ ነገር አለን” ማለታቸው ይታወሳል።
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፤ በኢትዮጵየ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሃት ከመንግስት ጋር ለመደራደር ሰባት ቅድመ ሁኔታ ማቅረቡን ተከትሎ ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፤ መንግስት እና ህወሃት እኩል ቁመና ላይ እንዳሉ ተደርጎ መታሰብ እንደሌለበት ተናግረዋል።
ቀርበዋል የተባሉት ቅድመ ሁኔታዎችም በሽብር ከተፈረጀ ቡድን መቅረብ የማይገባቸው መሆናቸውን ገልጸው፤ መንግስት ያወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ህወሃት በቅድሚያ መቀበል እንደነበረበትም ገልጸዋል።
ተጨማሪ ኮሪደር ይከፈት የሚል ጥያቄ ስለመቅረቡ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ያነሱት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአፋር ክልል ጉብኝት አድርገው እንደነበርም አረጋግጠዋል።