የሱዳኑ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በሜ/ጄ አብደል ባቂ በክራዊ የተመራ ነው ተባለ
ወታደሮቹ የሃገሪቱን ብሔራዊ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያን ለመቆጣጠር በሙከራ ላይ ነበሩም ነው የተባለው
በሜ/ጄ አብደል ባቂ በክራዊ የሚመሩት ወታደሮች በምስራቃዊ ሱዳን የሚገኘውን የሃሪቱን ጦር ተቆጣጥረው እንደበር ተገልጿል
ሱዳን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው በሜ/ጄ አብደል ባቂ በክራዊ የተመራ እንደነበር ገለጸች፡፡
በሜ/ጄ አብደል ባቂ በክራዊ የሚመሩትና የግልበጣ ሙከራው አካል የሆኑ ወታደሮች በምስራቃዊ ሱዳን የሚገኘውን የሃገሪቱን ጦር ተቆጣጥረው እንደበር ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
ወታደሮቹ ድልድዮችን መተላለፊያ መንገዶችን ይዘው እንደነበር የተገለጸም ሲሆን የሃገሪቱን ብሔራዊ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያን ለመቆጣጠር በሙከራ ላይ እንደነበሩም ተገልጿል፡፡
ጣቢያው መደበኛ ስርጭቱን አቋርጦ የተለያዩ ሃገራዊ ይዘት ያላቸውን ሙዚቃዎች ይለቅም ነበርም ተብሏል፡፡
ኦምዱርማንን ከሃገሪቱ ዋና ከተማ ካርቱም የሚያገናኘው ድልድይም በአሁኑ ወቅትም ተዘግቶ ይገኛል፡፡
ሆኖም የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው በቁጥጥር ስር መዋሉን የሚያመለክቱ መረጃዎችም እየወጡ ነው፡፡
የሃገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ቃል አቀባይም ይህንኑ ለአል ዐይን አረብኛ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል ሱዳናውያን ያመጡት ለውጥ እንዳይቀለበስ ወጥተው ይጠብቁ ሲሉ በይፋዊ የማህበራዊ ገጾቻቸው ጥሪ ያቀረቡት ቃል አቀባዩ መሃመድ ፈቂ ሱሌይማን “ነገሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል፤ አብዮቱም ባለድል” ሆኗል ብለዋል፡፡
ሆኖም ሙከራው አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን እና በወታደሮቹ ይዞታ ስር የሚገኙ ነገሮችም እንዳሉ የሚያመለክቱ ዘገባዎችም በመውጣት ላይ ናቸው፡፡
ከሰሞኑ በምስራቃዊ ሃገሪቱ አካባቢዎች አመጽ ተቀስቅሶ ነበር፡፡ አመጹ በቤጃ ጎሳ አባላት የተቀሰቀሰ ነበር፡፡
የጎሳ አባላቱ በምስራቅ ሱዳን ያሉ ወደቦችን ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍል ጋር የሚያገኘውን መንገድ ጭምር ዘግተው ነበር፡፡
ለተቃውሞ መነሻ የሆነው የቤጃ ጎሳ አባላት የሚኖሩበት ግዛት ኋላ ቀር ነው የሚል መሆኑን የተለያዩ ሚዲያዎች እየዘገቡት ይገኛሉ፡፡
የቤጃ ጠቅላይ ም/ቤት ተብሎ የሚጠራው የቤጃ ጎሳ አባላት ተቆርቋሪ ያሰማውን ጥሪ ተከትሎ ዋናው መንገድ አምስት ቦታዎች በላይ መዘጋቱ ተዘግቧል፡፡
ወደ ፖርት ሱዳንና ሱዋኪን ወደቦች የሚወስደው መንገድ በሬድሲ ግዛት አቃባን ጨምሮ በሶስት ቦታዎች ላይ የተዘጋ ሲሆን ከግብጽ ጋር የሚያገናኘው ኦሲፍ መንገድም በተቃውሞ መዘጋቱ ተገልጿል፡፡
ከሬድ ሲ ግዛት በተጨማሪ በከሰላ ግዛት በሁለት ቦታዎችና በገዳሪፍ ግዛት በሶስት ቦታዎች መዘጋቱም ተዘግቧል፡፡
ሱዳን በዳርፉር ተፈጽሟል ከተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር ስሟ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡