ፖለቲካ
ሁለተኛ ወሩን በጀመረው የሱዳን ግጭት ካርቱም የአየር ጥቃት ደረሰባት
የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ንጹሃንን ለመጠበቅ በጂዳ ስምምነት ላይ ቢደርሱም በካርቱም፣ ባህሪ እና ኦምዱርማን ከባድ ውጊያ ተካሂዷል
ካርቱም የጦሩና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ኢላማ መሆኗን ቀጥላለች
የሱዳን ጦር ወታደራዊ ተቀናቃኞቹን ለመግፋት በሰሜናዊ ካርቱም የአየር ድብደባ ማድረጉን እማኞች ተናግረዋል።
ምንም እንኳ በሳዑዲ እና በአሜሪካ አደራዳሪነት በጅዳ ሰብዓዊ ተደራሽነትን ለማስፈን እና ውጤታማ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም፤ በካርቱም እና በእህት ከተሞች ባህሪ እና ኦምዱርማን ከባድ ውጊያዎች ተካሂደዋል።
ጦርነቱ ወደ ምዕራባዊው የዳርፉር ክልል ተዛምቶ ቀድሞውንም ጠባሳ በሆነበት አካባቢ መድረሱ ቢነገርም፤ ግጭቱ በመዲናይቱ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።
በካርቱም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች በየአካባቢው እየሰፈሩ፤ ጦሩ ደግሞ ለማጥቃት የአየር ድብደባ እና ከባድ መሳሪያ እየተጠቀመ መሆኑ ተነግሯል።
የፈጥኖ ደራሹ መሪ መሀመድ ሃምዳን በጦርነቱ ተገድለዋል ወይም ተጎድተዋል የሚለውን ወሬ ውድቅ አድርገዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የሱዳን ግጭት 200 ሽህ የሚጠጉ ሰዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል። ከ700 ሽህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለዋል። ይህም ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል የተባለ ሲሆን፤ ግጭቱ ለቀጣናው አለመረጋጋትም አደጋ ደቅኗል።