የሱዳን ጦርነት 1 ወር ሆኖታል፤ ምን አበይት ክስተቶች ተስተናገዱ?
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) በመዲናዋ ካርቱም ጦር ከተማዘዙ አንድ ወር ሞልቷቸዋል
የጀነራል አልቡርሃን እና ጀነራል ዳጋሎ ግጭት መነሻና በጦርነቱ የታዩ አበይት ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
በ2019 ኦማር ሀሰን አልበሽርን ከ3 አስርት የስልጣን መንበራቸው በመፈንቅለ መንግስት ያነሱት የሱዳን ጀነራሎች ጦርነት ውስጥ ከገቡ አንድ ወር ሆኗቸዋል።
በሱዳን የሲቪል የሽግግር መንግስት ለመመስረት ሲደረግ የነበረው ድርድር የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉን ወደ ብሄራዊ ጦሩ የመቀላቀያ ቀነ ገደብ ማስቀመጡ ለግጭቱ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ቢጠቀስም ኩርፊያ እና የስልጣን ሽኩቻው የቆየ እንደሆነ ይነገራል።
5 ሚሊየን ነዋሪ ያላትን ካርቱም የጦር አውድማ ያደረገው የጀነራሎቹ ፍልሚያ ጅማሮ እና የታዩ ዋና ዋና ክስተቶችን እንዳስሳለን
ሚያዚያ 15 2023 - ካርቱም
በሚያዚያ ወር አጋማሽ ለሳምንታት ተካሮ የቆየው ውጥረት የሱዳን መዲና ካርቱምን በተኩስ ድምጽ መናጥ ጀምሯል።
በጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል በጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን መኖሪያ እና በካርቱም አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ሰነዘረ፤ የፕሬዝዳንቱን ቤተመንግስት እና የካርቱም ኤርፖርትንም በቁጥጥር ስር አስገብቻለሁ አለ።
የሱዳን ጦርም በአርኤስኤፍ ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባ በማድረግ መዲናዋን ሲንጣት ዋለ።
ሚያዚያ 16 2023
የአለም የምግብ ፕሮግራም ሶስት ሰራተኞቹ መገደላቸውን በመጥቀስ በሱዳን በጊዜያዊነት ስራ ማቆሙን ይፋ አደረገ። ድርጅቱ በግንቦት 1 2023 በድጋሚ ስራውን ሲጀመር 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሱዳናውያን ለረሃብ አደጋ እንደሚጋለጡ አስጠንቅቋል።
ሚያዚያ 18 2023
ተፋላሚዎቹ ሃይላት ለመጀመሪያ ጊዜ ተኩስ ለማቆም መስማማታቸውን ገለጹ። ይሁን እንጂ ስምምነቱን ወዲያውኑ ጥሰው ሚሊየኖች የኤሌክትሪክ፣ ውሃ እና ቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ተቋርጦባቸዋል።
ሚያዚያ 21 2023
ጀነራሎቹ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ የደረሱትን የተኩስ ማቆም ስምምነት ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን እና ይውጭ ሀገር ዜጎች ካርቱምን መልቀቅ ጀመሩ።
ሚያዚያ 22 2023
አሜሪካ በካርቱም ኤምባሲዋ የሚገኙ ሰራተኞችን በልዩ ዘመቻ አስወጣች፤ ፈረንሳይ እና ብሪታንያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በአየርና በየብስ ትራንስፖርት ዜጎቻቸውን ከሱዳን ማስወጣት ጀመሩ።
ሚያዚያ 25 2023
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ይገኙበት የነበረው የኮበር ማረሚያ ቤት በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ተሰብሮ እስረኞች አመለጡ፤ አልበሽር ከውጊያው በፊት ከማረሚያ ቤቱ ወጥተው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተነገረ።
ሚያዚያ 26 2023
ግጭቱ ከካርቱም አልፎ በኤል ጀኒና፣ ዳርፉር እና ሌሎች አካባቢዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ የባንኮች እና የንጹሃን ንብረት ዝርፊያውም እንዲሁ ተባብሷል።
ግንቦት 1 2023
ከ800 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ጦርነቱን ሽሽት ከቀያቸው እንደሚፈናቀሉ የመንግስታቱ ድርጅት ገለጸ፤ ቻድ፣ ደቡብ ሱዳን እና ግብጽን ጨምሮ ጎረቤት ሀገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ስደተኞችን እየተቀበሉ መሆኑንም አስታወቀ።
ግንቦት 3 2023
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባብሪያ ቢሮ ሃላፊው ማርቲን ግሪፍትስ ፖርት ሱዳን ገቡ፤ ከሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች መሪዎች ጋርም ፊት ለፊት ለመነጋገር እፈልጋለሁ አሉ።
ግንቦት 5 2023
ከ1 ሚሊየን በላይ የፖሊዮ ክትባት ከጥቅም ውጭ መሆኑን ዩኔሴፍ አስታወቀ።
ግንቦት 6 2023
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በጂዳ ድርድር ጀመሩ።
ግንቦት 9 2023
በሱዳን ከ700 ሺህ በላይ ዜጎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሆነዋል ሲል የአለም የፍልሰተኞች ድርጅት አስታወቀ። የሱዳን የባንኮች ዩኒየን በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸመውን ዝርፊያ አወገዘ።
ግንቦት 11 2023
ተፋላሚዎቹ በጂዳው ድርድር የሰብዓዊ እርዳታ መስመሮችን ለመክፈትና ንጹሀንን ለመጠበቅ ስምምነት ላይ ደርሰናል አሉ። ይህን ባሳወቁ እለት ግን ካርቱም በአየር ድብደባ ስትናጥ ዋለች።
ግንቦት 14 2023
በጂዳ ሁለተኛው ዙር ድርድር እንደሚቀጥል ተነገረ።
አንድ ወር የደፈነው የሱዳን ጦርነት ከ500 በላይ ንጹሃንን ለህልፈት ዳርጓል። ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሱዳናውያንን ወደ ጎረቤት ሀገራት ያሰደደው ጦርነት ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ እንደሚያስከትል የመንግስታቱ ድርጅት አስታውቋል።
በቀጣይ ስድስት ወራት ለምግብ ዋስትና ችግር የሚጋለጡ ሱዳናውያን ቁጥርም 19 ሚሊየን እንደሚደርስ ነው የተገለጸው።
አልበሽርን ለመጣልም ሆነ በ2021 በአብደላ ሃምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግስት ለመፈጸም ተናበው የሰሩት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃንም ሆኑ ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ግን አንድ ወር የሞላውን ጦርነት እስካሁን ማቆም አልፈለጉም።
ከሶስት ጊዜ በላይ የደረሷቸውን ተኩስ የማቆም ስምምነቶችም የጣሱ ሲሆን፥ ከጂዳው የመጀመሪያ ስምምነት በኋላም ግጭቱ ስለመቀጠሉ ከካርቱም የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ጀነራሎቹ በየፊናቸው ድል እንደሚቀናቸውና አንዱ አንዱን ካላሸነፈ በሱዳን ሰላም አይሰፍንም ብለው ማመናቸውም የሱዳናውያንን ሰቆቃ አብዝቶታል።
የተለያዩ ሀገራት ፍላጎትና ድጋፍም የጀነራሎቹን ጦርነት እንዳያረዝመው ስጋት አለ።
በኢጋድ በኩል የሚደረጉ ጥረቶችና በሳኡዲ አረቢያዋ ጂዳ ይቀጥላል የተባለው ሁለተኛ ዙር ድርድር የጠመንጃ ንግግሩን በፍጥነት የሚያስቆሙ ይሆኑ ዘንድ ሱዳናውያን በተስፋ እየተጠባበቁ ነው።