ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ አራት ጀነራሎችም ስራ እንዲያቆሙ ተወስኗል ተብሏል
የሱዳን ጦር መሪው ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የባንክ ሂሳብን አገዱ፡፡
የጎረቤት ሀገር ሱዳን እርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ አንድ ወር የሞላው ሲሆን በሳኡዲ አረቢያ የተጀመረው ድርድርም ብዙ ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡
በብሄራዊ ጦር እና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መካከል እየተደረገ ያለው ይህ ጦርነት እንዲቆም ኢጋድን ጨምሮ ምዕራባዊያን ሀገራት ቢያሳስቡም እስካሁን ጦርነቱ አልቆመም፡፡
ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የጀመሩትን ጦርነት እንዲያቆሙ በሳኡዲ አረቢያ እና አሜሪካ አማካኝነት ወደ ድርድር ቢመጡም ውጤት ማምጣት እንዳልቻሉ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ጀነራል አልቡርሃን የፈጥኖ ደራሽ ሀይል የባንክ ሂሳብ እንዲታገድ ወስነዋል ተብሏል፡፡
ጀነራል አልቡርሃን የባንክ ሂሳቡ እንዳይንቀሳቀስ ከመወሰናቸው በተጨማሪም በጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ወይም ሄሜቲ ከሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ጀነራሎችን ማገዳቸው ተገልጿል፡፡
ከታገዱት የጦር ጀነራሎች መካከልም ብርጋዴር ጀነራል ኦማር ሀምዳን አህመድ ሲሆኑ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይልን ወክለው በሪያድ እየተካሄደ ባለው ድርድር በመሳተፍ ላይ ነበሩ፡፡
እንዲሁም የሱዳን ብሄራዊ ባንክ ዋና ገዢ የሆኑት ሁሴን ሂያ ጃንኮልን ከስልጣን በማንሳት ቦራይ ኤል ሳዲቂን በምትካቸው መሾማቸው ነው የተነገረው፡፡
ጀነራል አልቡርሃን የብሄራዊ ባንክ ገዢውን ለምን ከስልጣን እንዳነሱ እስካሁን ያፋ ያላደረጉ ሲሆን የሱዳን ቴሌቪዥን ከአንድ ወር ስርጭት መቋረጥ በኋላም ወደ ስርጭት መመለሱ ተገልጿል፡፡