ቦርዱ ከክልሉ ውጭ ያሉ ሐረሪዎች የክልሉን ብሔራዊ ጉባኤ እንዲመርጡ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አደረገ
በባለፉት ሃገራዊ ምርጫዎች ከክልሉ ውጭ ያሉ ሐረሪዎች ድምጽ መስጠታቸው ይታወሳል
ቦርዱ ከሕገመንግስቱና ከሚተገብራቸው የምርጫ ሕግና መመሪያዎች አንጻር ጥያቄውን ተቀብሎ ለማስተናገድ እንዳልተቻለው አስታውቋል
ከሐረሪ ክልል ውጪ የሚኖሩ ሐረሪዎች በመጪው ሃገራዊ ምርጫ የክልሉ ምክር ቤት አካል ለሆነው የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ምርጫ ድምጽ እንዲሰጡ በሚል የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡
ጥያቄው ከክልሉ ውጭ ያሉ ሐረሪዎች ከአሁን ቀደም በተካሄዱት 5 ሃገራዊ ምርጫዎች ድምጽ መስጠታቸውን በማስታወስ በክልሉ ምር ቤት፣ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እና ብልጽግና ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበ ነበር፡፡
ጥያቄውን እንደሚያስረዳ በማሰብም የተወካዮች ም/ቤት በ1987 ዓ/ም የወሰነው ውሳኔ እና ቦርዱ ውሳኔውን ተከትሎ ጥያቄውን ያስፈጸመበት መመሪያም ጭምር ነበር ለቦርዱ ተያይዞ የቀረበው ለቦርዱ፡፡
ቦርዱም በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት መሠረት በአንድ ክልል የመንግስት አወቃቀር ውስጥ የሚገኙ ም/ቤት አባላት መመረጥ የሚኖርባቸው በክልሉ ድምፅ መስጠት በሚችሉ ነዋሪዎች ነው ሲል አስረድቷል፡፡
ከዚህ ውጭ ግን ሕገ መንግስቱ ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ ብሔረሰብ ለክልል ም/ቤቶች አባላት ሲያስመርጥ ከክልሉ ውጭ ያሉ የብሔረሰቡ አባላት እንዲመርጡ ለማስቻል የደነገገው ነገር የለም ብሏል፡፡
እንዲሁም ለብሔረሰብ አባላቱ ለብቻው የተለየ አሰራር ለመተግበር የሚያስችል ድንጋጌ በሕገመንግስቱ ላይ ባደረገው ምርመራ አለማግኘቱንም ነው ቦርዱ ያስታወቀው፡፡
እንዲሁም አቤቱታ አቅራቢዎቹ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት ተወካዮች ም/ቤት መጋቢት 6 ቀን 1987 ዓ/ም ባካሄደው 102ኛ መደበኛ ስብሰባ ሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ከክልሉ ውጭ ነዋሪ በሆኑ የብሔረሰቡ አባላት ይመረጣል የሚለውን ውሳኔውን የሚደግፍ የሕገ መንግስት አንቀጽ ጠቅሶ መወሰኑም በውሳኔው ላይ እንይማይታይ መረዳቱንም ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ይህ የም/ቤቱ 102ኛ መደበኛ ስብሰባ ሰጠ የተባለው ውሳኔ አግባብ ያለመሆኑን ከሚያሳዩት ሁኔታዎች አንዱ ሰነዱ በላዩ ላይ የም/ቤቱ ማህተም ያረፈበትም አይደለም፤ ይህም ሌላው የሰነዱን ተቀባይነት ችግር ውስጥ የጣለው ተጨማሪ ሁኔታ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ ብሏል።
በሌላ በኩል በዚህ የመጋቢት 6/1987 ተወካዮች ም/ቤት ውሳኔ መሠረት ቦርዱ ዝርዝር መመሪያ አውጥቶ እንደ ውሳኔው ያለፉትን አምስት ምርጫዎች ሲያስፈጽም እንደነበር ያሳያል የተባለውም የቦርዱ መመሪያ ከቦርዱ ጽ/ቤት ለማግኘት እንዳልቻለም አስታውቋል፡፡
ላለፉት 5 ምርጫዎች የብሔረሰቡን አባላት ሲያስመርጥ ቢቆይም አሁን በማድረግ ላይ ያለው ማሻሻያ (ሪፎርም) ዓላማ እንደዚህ ዓይነት የሕገመንግስትና የምርጫ ሕጉ መሠረት የሌላቸውን ልምዶችና አሰራሮች እንዳይቀጥሉ ለማድረግ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡
ጥያቄውን ተቀብዬ ለመቀጠል ብወስን እንኳን ሌሎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ብሔረሰቦች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ልፈጽም አልችልም ያለው ቦርዱ ምርጫውን በፍትሐዊነት እና በገለልተኛነት የማስተዳደሩን ጉዳይ አደጋ ላይ እንዲወድቅ እንደሚያደርግም ገልጿል፡፡
በመሆኑ ምርጫው ፍትሐዊ እንዲሆን ለሁለም በእኩል የሚያገለግልበት ሥርዓት ለመዘርጋት የግድ በሕገመንግስቱ ድጋፍ ያላቸውን እና አስቀድሞ ያሉ ልምዶችንና አሰራሮችን ብቻ ለመውሰድ እንደሚገደድ ነው የገለጸው፡፡
በዚህም ከሕገመንግስቱና ከሚተገብራቸው የምርጫ ሕግና መመሪያዎች አንጻር ይህን ጥያቄ ተቀብሎ ለማስተናገድ እንዳልተቻለውም አስታውቋል፡፡