“ንጉሣውያን ቤተሰቦቹ የልጄ የቆዳ ቀለም ያሳስባቸው ነበር”- ሜጋን ሜርክል
በቤተሰቡ ውስ ባይተዋርነት ይሰማት እንደነበር የገለጸችው ሜርክል ራሷን ስለማጥፋት ታስብ እንደነበርም ገልጻለች
ልዑል ሃሪና እና ባለቤቱ ከልዑላውያኑ ጋር የነበራቸውን ቆይታ አማረዋል
የዩናይትድ ኪንግደም ንጉሳውያን ቤተሰብ አባል የነበረው ልዑል ሃሪ እና ባለቤቱ ልዕልት ሜጋን ሜርክል በቤተሰቡ ውስጥ የነበራቸውን ቆይታ አማረዋል፡፡
ጥንዶቹ ሲቢሲ ቴሌቪዠን ላይ በሚተላለፈው የኦፕራ ዊንፍሪ ሾው ላይ ባደረጉት ቆይታ ከተጋቡበት ዕለት ጀምሮ በቤተሰቡ ጫና ይደርስባቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ሜጋን በቤተሰቡ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ ባይተዋርነት ይሰማኝ ነበር ብላለች፡፡ ይህንን ተከትሎ ራሷን ስለማጥፋት ታስብ እንደነበርም ነው በፕሮግራሙ የገለጸችው፡፡
ይህን ለሃሪ ለመንገር ጭምር ፈርቼ ነበር የምትለው ጥቁር አሜሪካዊቷ ተዋናይ ሜጋን ጉዳዩን ለባለቤቷ ባትነግረው ኖሮ ራሷን ልታጠፋ ትችል እንደነበር ተናግራለች፡፡
ከዚህ ባለፈም ነፍሰ ጡር በነበረችበት ወቅት የሚወለደው ልጅ ቀለም ጉዳይ ንጉሳውያን ቤተሰቡን በእጅጉ ያሳስባቸው እንደነበር ነው ያነሳችው፡፡ ይህን ጉዳይ ልዑል ሃሪ ጭምር አረጋግጦታል፡፡ ይሁንና ይህን የቆዳ ቀለም ጉዳይ ማን እንደተናገረው ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡
በንጉሳውያኑ ስነ ስርዓት በታጀበው የጋብቻ ስነ ስርዓታቸው ላይ ላይ አልቅሳ ነበር መባሉን ግን ሜጋን አስተባብላለች፡፡ እውነት እንዳልሆነም ነው የገለጸችው፡፡
ጥንዶቹ ቃለ ምልልስ ከሰጡ በኋላ በብሪታኒያ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ትችት እየደረሰ መሆኑን ሲኤን ኤን ዘግቧል፡፡ ትችቱ በዋናነት ከጥቁር አሜሪካውያን እና ከሌሎችም እየተሰነዘረ እንደሆነም ነው የተሰማው፡፡
ልዑል ሃሪ ሜጋን ለማግባት ወስኖ በነበረበት ጊዜም ቢሆን ከንጉሳውያን ቤተሰቦቹ ጫና እንዳላመለጠ ይነገርም ነበር፡፡