የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ካሚኒ ለሄዝቦላ መሪ ነስረላህ ከመገደሉ ከቀናት በፊት የላኩለት መልእክት ምን ነበር?
የካሚኒን መልእክት ያደረሰው ከነስረላህ ጋር የተገደለው ከፍተኛ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ አባል የሆነው ብርጋዴር ጀነራል አባስ ኒልፎሮሺያን ነው
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ ከመገደሉ ከቀናት ሊባኖስን ለቆ እንዲሸሽ የሄዝቦላን መሪ ነሰረላህን አስጠንቅቀውት እንደነበር ተዘገበ
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ካሚኒ ለሄዝቦላ መሪ ነስረላህ ከመገደሉ ከቀናት በፊት የላኩለት መልእክት ምን ነበር?።
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ ከመገደሉ ከቀናት ሊባኖስን ለቆ እንዲሸሽ የሄዝቦላን መሪ ሰኢድ ሀሰን ነሰረላህን አስጠንቅቀውት እንደነበረ ሮይተርስ ዘግቧል።
ካሚኒ አሁን ላይ እስራኤል በከፍተኛ የኢራን የመንግስት መስሪቤቶች ውስጥ ስርጎገብ ሳታሰማራ አትቀርም የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ዘገባው ጠቅሷል።
እንደዘገባው ከሆነ ካሚኒ ባለፈው መስከረም "ፔደር' በተባለው የሄዝቦላ የመገናኛ መሳሪዎች ላይ ፍንዳታ ከተከሰተ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ የደህንነት መረጃዎችን በመጥቀስ እስራኤል በሄዝቦላ ቡድን ውስጥ አስተኳሾቹ እንዳሏት እና ልትገድለው እንዳቀደች ለሄዝቦላ መሪ ነስረላህ የማሳሳቢያ መልእክት ልከውለት ነበር።
የካሚኒን መልእክት ያደረሰው ከነስረላህ ጋር ከመሬት ባለ መሸሸጊያ ወይም በንከር ውስጥ የተገደለው ከፍተኛ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ አባል የሆነው ብርጋዴር ጀነራል አባስ ኒልፎሮሺያን ነው።
ከባለፈው ቅዳሜ ጀሞሮ ኢራን ውስጥ ባልታወቀ ቦታ ያሉት ካሚኒ ባለፈው ቅዳሜ በእስራኤል ላይ 200 ሚሳይሎች እንዲተኮሱ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ኢራን ይህን ጥቃት የፈጸመችው የነስረላህን እና የኒልፎሮሺያንን ግድያ ለመበቀል መሆኑን አብዮታዊ ዘብ ጠባቂው ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።
መግለጫ እስራኤልን ተጠያቂ ያደረገበትን ባለፈው ሐምሌ ወር በሀማስ የፖለቲካ መሪ ሀኒየህ ላይ ቴህራን ውስጥ የተፈጸመውን ግድያ እና እስራኤል በሊባኖስ ላይ የከፈተችውን ጥቃት ጠቅሷል። እስራኤል ለሀኒየህ ግድያ በይፋ ኃላፊነት አልወሰደችም።
እስራኤል ባለፈው ማክሰኞ በሊባኖስ ላይ "የተወሰነ" ያለችውን የእግረኛ ጦር ጥቃት ከፍታለች።
እስራኤል በነስረላህ ላይ ግድያ የፈጸመችው ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት ባደረገችው መጠሰፊ የአየር ጥቃት የመሳሪያ ማከማቻዎችን፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን የሄዝቦላ ካውንስል አመራሮችን እና ከፍተኛ ወታደራዊ እዙን ካሽመደመደች በኋላ ነው።
ኢራን አሁን ላይ የካሚኒ ደህንነት እና የሄዝቦላ ከሰርጎገቦች ነጻ የመሆን ጉዳይ አስግቷታል። በ1980ዎቹ በኢራን ድጋፍ የተቋቋመው ሄዝቦላ ኢራን በምትመራው ጸረ-እስራኤል ጥምረት ውስጥ ጠንካራ አባል ሆኖ ለአመታት መዝለቅ የቻለ ነው።
ይህ ችግር ሰርጎገቦች የተተኪውን መሪ ህይወት አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ በሚል ስጋት ሄዝቦላ አዲስ መሪ ለመምረጥ እንደተቸገረ ሮይተርስ የሊባኖስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
እስራኤል ኢራን ለፈጸመችባት የሚሳይል ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ "ኢራን ከባድ ስህተት ሰርታለች፣ ዋጋ ትከፍላለች" ብለዋል።
ኢራን በበኩሏ እስራኤል ጥቃት የምትከፍትባት ከሆነ ከእስከዛሬው የከፋ እርሞጃ እወስዳለሁ ሰትል የማስጠንቀቂያ ምላሽ ተሰጥታለች።
የእስራኤል-ሊባኖስ ጦርነት ኢራንን እና የእስራኤል ዋነኛ አጋር የሆነችውን አሜሪካን ጎትቶ ወደ ጦርነቱ እንዳያስገባ ተሰግቷል።