እስራኤል ሀሰን ናስራላህን ለመግደል ያካሄደችው ሚስጢራዊ ዘመቻ ምን ይመስላል?
የእስራኤል የጦር ጄቶች የሄዝቦላህ መሪዎች ከሀገር እንዳይወጡ ለቀናት ሲጠባበቁ ቆይተዋል ተብሏል
ሀሰን ናስራላህና ሌሎች የሄዝቦላህ መሪዎች በቤሩት ወደሚገኘው የቡድኑ ቢሮ እንዲያመሩም አሳሳች መረጃዎች ሲወጡ ነበር
እስራኤል የሄዝቦላህ መሪዎችን ለመግድል ለአመታት ስትዘጋጅ ቆይታለች።
ባለፉት ሳምንታት በተለይም ባለፉት ቀናት ግን የአመታት ጥረቷ የሚሳካበትን እድል እንደፈጠረላት ገልጻለች።
የሄዝቦላህ አባላት የሚጠቀሙባቸውን የሬዲዮ መገናኛዎች በማፈንዳት የጀመረችው ልዩ ዘመቻ የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህና ሌሎች የቡድኑን ከፍተኛ መሪዎች እስከመግደል እንዳደረሳት ነው ያስታወቀችው።
የናስራላህ ግድያ እንዴት ተፈጸመ?
የእስራኤል ጦር እና የስለላ ድርጅቱ (ሞሳድ) ያቀረቡት ሀሰን ናስራላህን የመግደል እቅድ በእስራኤል የጦር ካቢኔ የጸደቀው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ነው።
ካቢኔው ለጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ለመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት እቅዱ ይፈጸም ዘንድ ፈቃድ ቢሰጥም ምንም መረጃው አላፈተለከም።
የሄዝቦላህ አመራሮችን ግራ ለማጋባትም ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ረቡዕ ምሽት ለመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ወደ አሜሪካ እንደሚያቀኑ በመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እንዲሰሩ ተደረገ። ይሁን እንጂ ኔታንያሁ ወደ ኒውዮርክ ያቀኑት ሀሙስ እለት ነበር።
ኔታንያሁ በመንግስታቱ ድርጅት አዳራሽ ንግግር ለማድረግ ከመግባታቸው ከጥቂት ስአታት በፊት ወሳኝ መረጃ ደርሷቸዋል፤ ሀሰን ናስራላህ በቤሩት በምድር ውስጥ ወደሚገኘው የሄዝቦላህ ዋና ቢሮ እየገቡ መሆኑን የሚያረጋግጥ መረጃ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉጉት የሚጠብቁት ጉዳይ ተፈጻሚ እንዲሆን “አዲስ ስርአት” የሚል ስያሜ የሰጡት ዘመቻ እንዲካሄድ አዘው ነው በ79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር ያደረጉት።
በዚያው ወቅት በቴል አቪቭ በሚገኘው የአየር ሃይል ማዘዣ የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት እና የእስራኤል ጦር ጠቅላይ አዛዥ ሄርዚ ሃሌቪ በቤሩት ለሚያንዣብቡ የእስራኤል የጦር ጄት አብራሪዎች ዝግጁ እንዲሆኑ አሳሰቡ ይላል የእስራኤሉ ዬዲዮዝ አሮኖዝ ጋዜጣ።
የጦር ጄቶቹ ሀሰን ናስራላህ እና ሌሎች አመራሮች በደቡባዊ ቤሩት ወደሚገኘው የቡድኑ ቢሮ መግባታቸውን እንዳረጋገጡም መሬት ሰንጥቀው የሚገቡ ቦምቦችን ማዝነባቸውንም ይጠቅሳል።
አሜሪካ ሰራሽ “በንከር በስቲንግ” ቦምቦቹ እስራኤል በጋዛ የሃማስን ዋሻዎች ለማፈራረስ የተጠቀመችባቸው አይነት ናቸው ግዙፍ ህንጻዎችንና ከምድር በታች የተገነቡ መሸሸጊያዎችን የማውደም ሃይላቸው ከፍተኛ መሆኑ ተዘግቧል።
የእስራኤል ጄቶች የግድያ ሴራው መረጃ ምናልባት አፈትልኮ ወጥቶ የሄዝቦላህ መሪዎች ከሀገር እንዳይወጡም ለቀናት በሊባኖስ ሰማይ ሲያንዣብቡ መቆየታቸውም ነው የተሰማው።
ሄዝቦላህ የመሪውን ሀሰን ናስራላህ ህልፈት የሚያረጋግጥ መግለጫ አውጥቷል።