ተጠርጣሪው በሀገረሰላም ወረዳ ነው በፖሊስ የተያዘው
ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን በመጥለፍ የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነገረ።
የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮን ጠቅሶ ኢዜአ እንደዘገበው ተጠርጣሪው ሳጂን የኋላ መብራቴ በሀገረ ሰላም ወረዳ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ተጠርጣሪው ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ከፀጥታ ሀይል ለማምለጥ ሲል በሻፋሞ ጫካ ለጫካ ሲዘዋወር እንደነበረ ተገልጿል።
“ማንም ከህግ በላይ አይደለምና የፀጥታ ሀይሉ በተቀናጀ መንገድ ከበባ ውስጥ በማስገባት ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል” ያሉት የቢሮው ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ፥ ተጠርጣሪው አከባቢ በመቀየር ፍለጋውን አስቸጋሪ አድርጎት መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ማህበረሰቡን በማሳተፍ በተደረገው አሰሳ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ከ40 ደቂቃ ላይ በሀገረ ሰላም ወረዳ በቁጥጥር ስር መዋሉን አረጋግጠዋል።
ተጠርጣሪው ግለሰብ ወንጀሉን ለመፈጸም ሲጠቀምባቸው ከነበሩ አንድ ክላሽንኮቭ የጦር መሳሪያና ሽጉጥ ጋር መያዙንም ነው አቶ አለማየሁ የተናገሩት።
በዳሽን ባንክ ሐዋሳ ዋርካ ቅርንጫፍ አካውንታት ሆና ስትሰራ የቆየችው ወይዘሪት ጸጋ፥ ግንቦት 15፣ 2015 አመሻሽ ላይ ከስራ ወደ ቤቷ ለማምራት ታክሲ የምትይዝበት ቦታ ላይ የመንግስት መኪና በያዘና አስቀድሞ ለፍቅር ጓደኝነት በሚፈልጋት ግለሰብ መጠለፏን አል ዐይን ቤተሰቦቿን አነጋግሮ መዘገቡ ይታወሳል።
በጠላፋው የተጠረጠረው ግለሰብ የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ ጠባቂ የነበረው ሳጂን የኋላ መብራቴ እንደሆነና የሚገኙበትን ስፍራ ከስራ ባልደረባዋ የሰሙት ቤተሰቦቿ ወደ ሀገረ ሰላም በማቅናት ቢፈልጓትም ሊያገኙት ሳይችሉ ቀርተዋል።
ግለሰቡ በሚደርሰው መረጃ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ ፍለጋውን አስቸጋሪ እንዳደረገውና ለማግባት እየተሰናዳች የነበረችውን ጸጋ በላቸው ሽማግሌ በመላክ ሊያገባት እንደሚፈልግ፤ ይህ ካልሆነ ግን እንደሚገድላት ጭምር ሲዝት መቆየቱንም ቤተሰቦቿ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረው ነበር።
የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር አደረግኩት ባለው ዘመቻ ግለሰቧን ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ማስለቀቅ መቻሉን ባለፈው ሳምንት መግለጹ ይታወሳል።
በዛሬው እለትም መላው ኢትዮጵያውያንን ካነጋገረው የጠለፋ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠረው ግለሰብ መያዙ ተገልጿል።
የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ የጠለፋ ወንጀል የተፈጸመባት ወይዘሪት ፀጋ በላቸው በፍትህ ስርዓቱ እንድትካስና ተጠርጣሪው እና ግብረአበሮቹ ተገቢውን የህግ ቅጣት እንዲያገኙ እሰራለሁ ብሏል።