በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ከ22.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መታቀፋቸው ተገለጸ
በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ከ22.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መታቀፋቸውን የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛን ኪሮስ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በ2011 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን እንቅስቃሴ በ5 ክልሎች እና በአንድ የከተማ አስተዳደር በሚገኙ 657 ወረዳዎች ተጀምሮ 509 ወረዳዎች ቅድመ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ለአባላቶቻቻውና ቤተሰቦቻቸው የህክምና አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል፡፡ በነዚህ ወረዳዎች የሚኖሩ ከ22.5 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎችም በጤና መድህን ስርዓቱ ታቅፈዋል፡፡
በጤና መድህን ስርዓቱ ከታቀፉት ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና አመታዊ የጤና መድህን መዋጯቸውን መክፈል የማይችሉ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የጤና መድህን መዋጯቸው በመንግስት እንዲሸፈንላቸው ተደርጓል ብለዋል፡፡
በ2011 በጀት ዓመት ከማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የአባላት መዋጮ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቁመው፣ የጤና መድህን አባላትና ቤተሰቦቻቸው በጤና መድህኑ ላገኙት የህክምና አገልግሎት ከ 617 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈፀሙንም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛን ኪሮስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የ2012 የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት የአባልነት ምዝገባና ዕድሳት መርሃግብር ከታህሳስ ወር ጀምሮ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የጤና መድህን አባል የሆኑ ሰዎችን የአባልነት ዕድሳት እንዲሁም አዳዲስ አባላትን ወደ ጤና መድህኑ የማስገባት ስራ በየክልሎቹ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የአባልነት ምዝገባና የዕድሳት ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊትም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተግባራዊ በተደረገባቸው ክልሎች የሚገኙ ዜጎች ለጤና መድህን አባልነት የሚጠበቀውን ዓመታዊ መዋጮ በመክፈል እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበው፣ የጤና መድህን አባል የሆኑ ዜጎችም አባልነታቸውን በማደስ እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በመግለጫው ጥሪ ቀርቧል፡፡
ለማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ትግበራ ስኬት ከፍተኛ ሚና ያላቸው ክልሎች፣ የጤና ሴክተር ባለድርሻ አካላት፣ ዞኖችና ወረዳዎች ነዋሪዎቻቸውን በጤና መድህን ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመሩትን የንቅናቄ ዘመቻ አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት በገጠርና በከተሞች አካባቢ መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ፣ በእርስ በርስ የመደጋገፍ መርህ መሰረት በተናጠል ሊፈጠር የሚችለውን ከፍተኛ የጤና ወጪ ጫና በማስቀረት ቤተሰቦች ወደ ከፋ ድህነት እንዳይገቡ የሚታደግ ስርዓት መሆኑንም ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል ሲል ኤጀንሲው በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ አስታውቋል፡፡