የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በፍልስጤም ሀገርነት መፍተሄ ላይ አለም አቀፍ ጉባኤ እንዲካሄድ ጥሪ አቀረበ
ድርጅቱ በትላንትናው እለት ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ፍልስጤም ነጻ ሀገር ሆና መመስረትን የሚያፋጥን የውሳኔ ሀሳብ ላይ ድምጽ ሰጥቷል
የውሳኔ ሀሳቡን አሜሪካ እና እስራኤልን ጨምሮ 8 ሀገራት ሲቃወሙት በአብላጫ ድምጽ ድጋፍ አግኝቷል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ፍልስጤም ሀገር ሆና እንድትመሰረት የሚረዳ የውሳኔ ሀሳብ አጽቋል።
ድርጅቱ ትላንት ባካሄደው ጉባኤ ያጸደቀው የውሳኔ ሀሳብ እስራኤል በፍልስጤም ግዛቶች ላይ የምታደርገውን የይዞታ መስፋፋት እንድታቆም እና ፍልስጤም ነጻ ሀገር ሆና እንድትመሰርት የሚጠይቅ ነው፡፡
በፍልስጤም ጉዳይ የአመታዊ ግምገማ አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባኤ የውሳኔ ሀሳቡ በ157 አባላት አብላጫ ድምጽ ድጋፍ ያገኝ ሲሆን እስራኤል፣ አሜሪካ፣ ሃንጋሪ እና አርጀንቲናን ጨምሮ 8 አባላት ሲቃወሙት 7 አባላት ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል፡፡
ውሳኔው በቅድመ 1967 ስምምነት መሠረት በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላምና ፀጥታ የሰፈነበት የድንበር መስመር ተሰምሮላቸው በአለም አቀፍ ህግ 'ቱ ስቴት ሶሉሽን' ወይም ከእስራኤል ጎን ፍልስጤም ሀገር እንድትሆን የሚጠይቀውን ሀሳብ እንደሚደግፍ አረጋግጧል፡፡
በተጨማሪም በመካከለኛው ምስራቅ ሰላምን ለማስፈን የተጀመሩ ሂደቶች ተአማኒነት ያለው ድርድር በማከናወን ጦርነቱን ለመቋጨት አስቸኳይ የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል፡፡
የውሳኔ ሃሳቡ የሁለት ሀገርነት መፍትሄን ተግባራዊ ለማድረግ በመጪው ሰኔ ወር አለም አቀፍ ጉባኤ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ለዚህም ጠቅላላ ጉባኤው የፍልስጤም ጥያቄ ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ የመፍትሄው አፈጻጸም ላይ ለመምከር በፈረንሳይ እና ሳኡዲ አረብያ የሚመራ ከፍተኛ አለም አቀፍ ጉባኤ እንዲጠራ ወስኗል።
አለም አቀፍ ጉባኤው ከአለም አቀፍ ህግ ጋር የማይጣጣሙ የግዛት መስፋፋቶችን ለማስቆም ፣ ሁለቱ ወገኖች በህግ ላይ የተመሰረተ የጸና ስምምነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ቀደም ሲል የገቡትን ስምምነቶች እና ቃል ኪዳኖች እንዲያከብሩ እና ለአሁናዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማስቀመጥ ያግዛል ተብሏል፡፡
ከሁሉም በላይ የፍልስጤም ህዝቦች ሉዐላዊነት እንዲከበር የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸው እና ነፃ ሀገር የመመሥረት መብታቸው እንዲከበር ያስችላል ነው የተባለው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የአለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እስራኤል በፍልስጤም ግዛቶች የምታደርገውን የግዛት መስፋፋት በፍጥነት እንዲያስቆም በአካባቢው ያሰፈረቻቸውንም ዜጎች እንድትታስወጣ ህጋዊ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቋል፡፡
ምስራቅ እየሩሳሌም ፣ ዌስት ባንክ እና በጋዛ ሰርጥ እስራኤል አዳዲስ ቦታዎችን እየያዘች እንደምትገኝ ጠቅላላ ጉባኤው አስታውቋል፡፡