እስራኤል ከሄዝቦላ ከፍተኛ ውጊያ እያካሄደች መሆኗን አስታወቀች
በእግረኛ ጦር ሊባኖስ ግዛት ውስጥ የወረረችው እስራኤል ከሄዝቦላ ከፍተኛ ውጊያ እያካሄደች መሆኗን አስታወቀች
የእስራኤል ጦር ውጊያ እያካሄዱ ለሚገኙት ወታደሮች የአየር ኃይል እና የከባድ መሳሪያ ሽፋን እየተሰጣቸው ነው ብሏል
በእግረኛ ጦር ሊባኖስ ግዛት ውስጥ የወረረችው እስራኤል ከሄዝቦላ ከፍተኛ ውጊያ እያካሄደች መሆኗን አስታወቀች
በደቡብ ሊባኖስ ወረራ የመጀመረው የእስራኤል ልዩ ኃይሏ እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሏ ከሄዝቦላ ጋር ከፍተኛ ውጊያ እያካሄደ መሆኑን እስራኤል አስታውቃለች።
የእስራኤል ጦር የሊባኖስ ዘመቻ የተጀመረው ሰኞ ምሽት መሆኑን እና በዘመቻው በጋዛው ጦርነት ከሀማስ ጋር ለወራት ሲዋጋ የነበረውን ወደሰሜን ግንባር የተላከውን 98ኛ ክፍለጦርን ማካተቱን ገልጿል።
ጦሩ እንደገለጸው "የተወሰነ፣ አካባቢያዊ፣ ኢላማ ያለው የእግረኛ ጦር ወረራ" እያካሄዱ ለሚገኙት ወታደሮች የአየር ኃይል እና የከባድ መሳሪያ ሽፋን እየተሰጣቸው ነው ብሏል።
ሮይተርስ ሁለት የሊባኖስ የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ የእስራኤል ኃይል ለቅኝት እና ዘመቻውን ለመምራት ወደ ሊባኖስ አቋርጠው የገቡት በትናንትናው እለት ነው። የሊባኖስ ወታደሮችም ከድንበር ምሽጋቸው ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
ሄዝቦላ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ እስራኤል ውስጥ የሚገኙ የእስራኤል ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ የሮኬት እና የከባድ መሳሪያ ጥቃት መሰንዘሩን ገልጿል። ነገርግን ሄዝቦላ የእስራኤል ወታደሮች ሊባኖስ ውስጥ መግባታቸውን በመግለጫው አልጠቀሰም።
ከሊታኒ ወንዝ በስተደቡብ የሚገኘውን ሄዝቦሃ ማጥፋት እንደምትፈልግ ገልጻ የነበረችው እስራኤል ሊባኖሳውያን ከወንዙ ሰሜናዊ አቅጣጫ ወደ ደቡብ ክፍል በመኪና እንዳይንቀሳቀሱ አስጠንቅቃለች።
እስራኤል ባለፈው ሳምንት አርብ እለት በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሄዝቦላ መሪ የሆነውን ሀሰን ነሰረላህን በመግል በመካከለኛው ምስራቅ የኢራን ኃያል አጋር በሆነው ቡድን ላይ ከባድ ኪሳራ አድርሳለች።
እስራኤል በዚህ ዘመቻ ማሳካት ከፈለገቻቸው ግቦች ዋነኛው የሄዝቦላን የሮኬት ጥቃቶች ሸሽተው የነበሩትን በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የሰሜን እስራኤል ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው መመለስ ነው።
እስራኤል በሊባኖስ ላይ የእግረኛ ጦር ወረራ ማካሄድ የጀመረችው "ፔጀር" በተባለ የሄዝቦላ የመገናኛ መሳሪያ ላይ ፈንጅ አጥምዳ ካፈነዳች እና የሄዝቦላ መሪ የተገደለበትን የባለፈው አርቡን ጨምሮ ለሁለት ሳምንታት የአየር ጥቃት ካደገች በኋላ ነው።
እስራኤል በፈጸመችው ከባድ የአየር ጥቃት በርካታ የቡድኑ መሪዎችን ማስወገድ የቻለች ቢሆንም በንጹሃን ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል።
በቤሩት በተፈጸሙ ተከታታይ የእስራኤል የአየር ጥቃት 1000 ገደማ ንጹሀን የተገደሉ ሲሆን በ100ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በስጋት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።