ሩሲያ ኢኮዋስ በኒጀር ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዳይወስድ አስጠነቀቀች
ኢኮዋስ በኒጀር ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ተጠባባቂ ሀይሎች ዝግጁ እንዲሆኑ ትዕዛዝ አስተላልፏል
በኒጀር በተካሄደ መፈንቅለ መንግሥት ወታደራዊ ቡድኑ ስልጣን መቆጣጠሩ ይታወሳል
ሩሲያ ኢኮዋስ በኒጀር ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዳይወስድ አስጠነቀቀች።
የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኒጀር ከሁለት ሳምንት በፊት በተፈጸመ መፈንቅለ መንግሥት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዙም ከስልጣን መነሳታቸው ይታወሳል።
የፕሬዝዳንቱ ጥበቃ ሀላፊ የነበሩት ጀነራል አብዱራህማን ቲያኒ ደግሞ ራሳቸውን የሀገሪቱ መሪ አድርገዋል።
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወይም ኢኮዋስ በናይጀሪያ መዲና አቡጃ ባደረገው ስብሰባ ስልጣን የተቆጣጠረው ቡድን ስልጣኑን ለፕሬዝዳንት ባዙም ካላስረከበ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
ይህን ተከትሎ ሩሲያ ኢኮዋስ በኒጀር ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዳይወስድ ማስጠንቀቋ ተገልጿል።
ኢኮዋስ ወታደራዊ እርምጃ የሚወስድ ከሆነ ኒጀር እና አካባቢው ሀገራትን ወደ ተባባሰ ቀውስ ሊያስገባ እንደሚችል ሩሲያ አስጠንቅቃለች።
ሩሲያ በይፋ የኒጀርን መፈንቅለ መንግሥት ያልደገፈች ሲሆን አሜሪካ እና ፈረንሳይ ግን ሞስኮ በዋግነር በኩል የኒጀርን አለመረጋጋት ለመጠቀም እየሞከረች ነው ብለዋል።
ፓሪስ እና ዋሽንግተን ስልጣን የተቆጣጠረው የኒጀር ወታደራዊ ቡድን ስልጣኑን ለፕሬዝዳንት ባዙም እንዲያስረክብ በማሳሰብ ላይ ናቸው።
አሜሪካ እና ፈረንሳይ በምዕራብ አፍሪካ ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚል በኒጀር ወታደሮቻቸውን አስፍረዋል።
በዓለም ዩራኒየም ማዕድን ባለጸጋ የሆነችው ኒጀር የአውሮፓ ሀገራት በተለይም የፈረንሳይ ዋነኛ ደንበኛ ሀገርም ናት።