ኢኮዋስ ወታደራዊን ጨምሮ ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች መንግስትን ገልብጦ ስልጣን በያዘው የኒጀር ወታደራዊ ጁንታ ላይ እርምጃ ለመውሰድ በናይጀሪያ በዝግ ተቀምጠዋል።
ምክክሩ ጁንታው ዲሞክራሲን እንዲመለስ የቀረበለትን ምርጫ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ነው።
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ወታደራዊ መንግስቱ ስልጣንን ለማስረከብ አሻፈረኝ ካለ የኃይል እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
በናይጀሪያ አቡጃ የተጀመረው ስብሰባ ለውጥረቱ መፍትሄ ለማበጀት ሁነኛ ስፍራ ሊኖረው እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል።
የህብረቱ መሪዎች ወታደራዊ እርምጃን ጨምሮ ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ይስማማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢኮዋስ ሹማምንት ወታደራዊ እርምጃዎችን እንደ መጨረሻ አማራጭ መያዛቸው ተነግሯል።
መንግስት ገልባጩ ምንም እንኳ ቀጣይ መንግስታዊ እቅዱን ባያሳውቅም አዲስ ጠቅላይ ሚንስትርን ጨምሮ 21 ሚንስትሮችን ለኒጀር ሾሟል።
ሦስቱ የመፈንቅለ መንግስቱ አቀናባሪዎች የመከልከያ፣ የሀገር ውስጥና የስፖርት ሚንስትር ሆነዋል።