ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የተጣለባቸው ቅጣት ምን ያህል ነው?
ሜታ፣ ኤክስ (ትዊተር) እና አፕልን ጨምሮ ዋናዋና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከመረጃ አያያዝ ጋር በተያያዘ የተጣለባቸውን ቅጣት አልከፈሉም ተብሏል
በቴክኖሎጂ ኩባንያዎቹ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድም እየተጠየቀ ነው
የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከመረጃ አያያዝ ክፍተት፣ ተቀናቃኞቻቸውን ከገበያ ውጭ ለማድረግ በወሰዷቸው እርምጃዎች እና ዋጋ ካለማስተካከል ጋር በተያያዘ በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
ይሁን እንጂ ኩባንያዎቹ የተጣለባቸውን ቅጣት እስካሁን አለመክፈላቸውን የአየርላንድ የመረጃ ቁጥጥር ባለስልጣን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጿል፡፡
የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ በዚህ አመት ከመስከረም ወር ወዲህ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ቅጣት እንዲከፍል በተለያዩ ሀገራት ውሳኔ ተላልፎበታል።
አማዞንም ከ2021 ጀምሮ የ746 ሚሊየን ዶላር ቅጣት ቢጣልበትም እስካሁን አልከፈለም ተብሏል።
የሉግዘንበርግ የመረጃ ቁጥጥር ባለስልጣን እንዳስታወቀው አማዞን ውሳኔውን ተቃውሞ ይግባኝ እንደሚጠይቅ በማሳወቅ ቅጣቱን ከመክፈል ተቆጥቧል።
የአልፋቤቱ ጎግልም ከ2017 እስከ 2019 በአውሮፓ ህብረት የተላለፈበትን ከ8 ቢሊየን ዩሮ በላይ ቅጣት እስካሁን መክፈል አልቻለም ነው የተባለው።
አፕል በበኩሉ በአየርላንድ (13 ቢሊየን ዩሮ) እና ፈረንሳይ (1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዩሮ) የተላለፈበትን ቅጣት ላለመክፈል ለአመታት ክርክሩን መቀጠሉ ተገልጿል።
ኤክስ (ትዊተር) በህጻናት ላይ የሚደርሱ ወሲባዊ ትንኮሳዎችን የሚያመላክቱ ይዘቶችን ከገጹ ላይ ባለማንሳቱ በአውስትራሊያ የ610 ሺህ ዶላር ቅጣት ቢጣልበትም ክፍያውን ለመፈጸም አልፈቀደም።
የተላለፈባቸውን ቅጣት ያለመክፈል ችግር የአምስቱ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ችግር ነው ብሏል የአየርላንድ የመረጃ ቁጥጥር ባለስልጣን።
ሀገራት የተላለፉ ውሳኔዎችን በፍጥነት ተፈጻሚ ማድረግ ካልቻሉ የዲጂታል ሚዲያው ይበልጥ አደጋ ውስጥ ይወድቃል፤ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል የሚሉ ተሟጋቾችም ጠንከር ያሉ ውሳኔዎች ሊተላለፉባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኩባንያዎቹ ቅጣታቸውን መክፈል ካልቻሉ ይዘጉ የሚል አስተያየታቸውን የሚሰጡ አካላትም አልታጡም።
በቢሊየን ዶላር የሚያንቀሳቅሱትና ለሚሊየኖች የስራ እድል የፈጠሩት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ግን ጥፋተኛ አይደለንም በሚል የተጣለባቸውን ቅጣት ለማስነሳት መከራከርን መርጠዋል።