በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል እና ሱዳን ጦር መካከል አለመስማማት መኖሩ ተገለጸ
ጀነራል ሙሀመድ ሀምዳን በጦሩ ውስጥ በስልጣን ምክንያት አለመስማማት እንዳለ ተናግረዋል
በጦሩ አባላት መካከል ስልጣን ለሲቪል አስተዳድር ይሰጥ እና አይሰጥ የሚል አለመስማማት እንዳለ ተገልጿል
በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል እና ሱዳን ጦር መካከል አለመስማማት መኖሩ ተገለጸ።
በጎረቤት ሀገር ሱዳን በተፈጸመ መፈንቅለ መንግሥት ምክንያት እስካሁን ሀገሪቱ በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳድር ውስጥ ትገኛለች።
ይህን ተከትሎም ሱዳናዊያን ወታደራዊ መንግሥቱ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድር እንዲያስረክብ በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ስልጣን የተቆጣጠረው የሀገሪቱ ጦር ስልጣን ለሲቪል አስተዳድር አስረክባለሁ ማለቱን ተከትሎ ከሱዳን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት በመደረግ ላይ ነው።
ይሁንና በሱዳን የጸጥታ ሀይሎች መካከል ስልጣን ለሲቪል እናስረክብ እና አናስረክብም በሚል ለሁለት መከፈላቸው ተገልጿል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር መሪ እና የሀገሪቱ ምክትል ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት መሪ ሌተናንት ጀነራል ሙሀመድ ሀምዳን በተለምዶ ሀመድቲ የሚባሉት እንዳሉት " በጦሩ መካከል አለመስማማት አለ፣ አለመስማማቱም ስልጣን ለሲቪል አስተዳድር እናስረክብ እና አናስረክብ በሚሉ መካከል ነው" ብለዋል ሲል ኤፒ ዘግቧል።
ሄመድቲ አክለውም "እኛ አለመስማማት አንችልም፣ እኛ ስልጣን ለሲቪል አስተዳድር አናስረክብም ከሚሉት ጎራ አይደለንም፣ እኛ ስልጣን አናስረክብም እና አምባገነን መሆን ከሚፈልጉት በተቃራኒ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።
የሱዳን ጦር እና ሲቪል ፖለቲከኞች ባደረጉት ምክክር መሰረት ስልጣን ለነሱ እናስረክባለን ይህ ሊቀለበስም አይችልም ማለታቸውም ተገልጿል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ምክትል ኮማንደር አብዳል ራሂም ዳግሎ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ በሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መካከል መከፋፈል እንዳለ ተደርጎ የሚነዛው መረጃ ፈጽሞ ውሸት ነው ብለው ነበር።
የሀገሪቱን የጸጥታ ሀይል ለመከፋፈል እና የፖለቲካውን ውጥረት ለማባባስ ሆን ተብሎ የሚዲያ ዘመቻ መከፈቱንም ጠቅሰዋል።