"በኮቴ ክፍያ" የተማረሩት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች መፍትሄ የሚሰጣቸው ማጣታቸውን ተናገሩ
አሸከርካሪዎች ከጅቡቲ አዲስ አበባ እስከሚደርሱ ድረስ የሚጠየቁት የኮቴ ክፍያ እንዳማረራቸው ተናግረዋል
ከጂቡቲ አዲስ አበባ ድረስ በምናቋርጣቸው ከተሞች ከአስር ባላነሱ ቦታዎች ከ600 እስከ 2 ሺህ ብር ድረስ የኮቴ ክፍያ እንደሚጠየቁ አሽከርካሪዎች ገልጸዋል
"በኮቴ ክፍያ" የተማረሩት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች መፍትሄ የሚሰጣቸው ማጣታቸውን ተናግረዋል።
ከጅቡቲ አዲስ አበባ ጭነቶችን የሚያመላልሱ የደረቅ መኪና አሽከርካሪዎች በየመንገዱ ከሚያጋጥማቸው እገታ እና ዝርፍያ ባለፈ በተደጋጋሚ የሚጠየቁት የኮቴ ክፍያ ስራቸውን እንዳከበደባቸው ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
አሽከርካሪዎቹ ከጅቡቲ አዲስ አበባ እስከሚደርሱ ድረስ በሚያቋርጧቸው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ከ600 ብር እስከ 2 ሺህ ብር ድረስ እንደሚጠየቁ ለአል ዐይን አማረኛ ተናግረዋል፡፡
ብርሀኑ (ስሙ የተቀየረ) ለ12 አመታት ከጂቡቲ አዲስ አበባ እንዳሽከረከረ ይናገራል።
ቀደም ሲል በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ለልማት በሚል ሾፌሮች በፍቃደኝነት የሚከፍሉት ክፍያ እንደነበር አንስቶ በቅርብ ጊዜያት በተለያዩ ከተሞች አሽከርካሪዎች የሚጠየቁት የኮቴ ክፍያ መበርከት ሁኔታዎችን ስለማክበዱ ይናገራል፡፡
“በየከተሞች መግብያ ላይ ገመድ የወጠሩ የመዘጋጃ ቤት እና የከተማ ገቢዎች ቢሮ ሰራተኛ እንደሆነ የሚናገሩ ሰዎች ያስቆሙናል፤ ከዛም የኮቴ ትባላለህ አለፈነው በመጣነው ከተማ ላይ ክፍያ እንደከፈለን ስንናገር አሰራር ነው ክፈሉ እንባለለን” ሲል በምሬት ይናገራል፡፡
የኮቴ ክፍያ ሰብሳቢዎቹ ከሚሊሻ ታጣቂዎች ጋር በኬላዎች አካባቢ እንደሚቆሙ የሚናገረው ብርሀኑ ገንዘብ የለኝም ወይም አልከፍልም ማለት ከመኪና አስወርዶ እስከ ማስደብደብ እና ንብረት እስከማውደም እንደሚያደርስ ተናግሯል፡፡
“ከጂቡቲ አዲስ አበባ እስከምትደርስ ድረስ ከ10 ያላነሱ ቦታዎች ትጠየቃለህ አይሻ ፣ ድሬዳዋ ፣ ካራሚሌ ፣ ቆቦ፣ ቦረዳ፣ ሂድና ፣ ጭሮ ፣ ደበሶ እና ሞጆ ከተሞች በቋሚነት የኮቴ ክፍያ ከሚከፈልባቸው ቦታዎች መካከል ናቸው።
አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመንግስት አካላት ያልሆኑ ወጣቶች ጭምር ለከተማ ልማት በሚል በሀሰተኛ ደረሰኝ ከ20 ብር ጀምሮ ገንዘብ ሲሰበስቡ አጋጥመውኛል፡፡”
ገቢ የሚሰበሰብባቸው ኬላዎች ከመቀራረባቸው የተነሳ ለመተያየት በሚያስችል ርቀት ላይ እንደሚገኙ የሚነሳው ሰዒድ የተባለ ሌላ የደረቅ ጭነት መኪና አሽከርካሪ በበኩሉ ሁኔታውን አስከፊ የሚያደርገው ክፍያ በተጠየቅንባቸው አካባቢዎች በሙሉ የምንከፍለው ክፍያ ከኪሳችን መሆኑ ነው ይላል፡፡
“የተሸከርካሪዎቹ ባለንብረቶች በወጪ መልክ የሚያወራርዱልን አንድ ወይም ሁለት ደረሰኝ ቢሆን ነው ክፍያው በመብዛቱ የተነሳ ባለንብረቶቹ እምነት በማጣታቸው ሌላው ከሾፌሮች ገቢ ላይ የሚቀነስ ነው ይህ አሁን ባለው የኑሮ ሁኔታ ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን አስበው፡፡”
አሽከርካሪዎቹ ከሚጠየቁት የኮቴ ክፍያ ባለፈ ክፍያ ለመፈጸም የሚሰለፉት ሰልፍ የሚወስደው ጊዜ ረጅም መሆን ስራቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዳያከናውኑ እና በመንገድ ላይ የሚያጠፉት ጊዜ እንዲረዝም ከማድረጉ ባለፈ የምግብ እና ተያያዥ ወጪያቸው እንዲጨምር ምክንያት ስለመሆኑ ቅሬታቸውን ለአልአይን አማረኛ ተናግረዋል፡፡
ስራው በባህሪው ካለው አስቸጋሪነት ባለፈ በተደጋጋሚ የሚገጥማቸው ተግዳሮት ኑሯቸውን እንዳከበደው የሚናገሩት አሽከርካሪዎች መንግስት መፍትሄ እንዲያበጅላቸው ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ዘውዱ ተሸከርካሪዎቹ የሚያጓጉዙት የግንባታ እቃዎች ፣ መድሀኒት ፣ አልባሳት ፣ ምግብ ፣የመኪና መለዋወጫዎች እና ሌሎችም ለኢኮኖሚው ትልቅ አበርክቶ ያላቸውን ግብአቶች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
“አሽከርካሪዎቹ የመንግስት እና የህዝብ ሀብትን ለተጠቃሚው ለማድረስ በሚያደርጉት ጥረት በየከተሞቹ የኮቴ ክፍያ መጠየቃቸው ተገቢ አለመሆኑን ለሚመለከታቸው የገቢዎች እንዲሆም ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚንስቴር ሀላፊዎች አሳውቀን ለክልሎቹ ችግሩ እንዲቀረፍ ተቋማቱ ለክልሎቹ ደብዳቤ ቢጽፉም ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል” ብለዋል አቶ ሰለሞን።
በአሁኑ ወቅት ከአስር ባለነሰ ከተሞች የኮቴ ክፍያ እንደሚጠየቅ የሚነሱት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ከጂቡቲ አዲስ አበባ ባሉ 30 እና ከዛ በላይ ከተሞች ይህ አሰራር የሚስፋፋ ከሆነ ዘርፉን የሚጎዳ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ሸፎሬቹ እና ማህበሩ የነሱትን ቅሬታ እንዲሁም ስለህጋዊነቱ ከኦሮሚያ ክልል የገቢዎች ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ለመሆኑ የኮቴ ክፍያ ከህግ አንጸር ምን ያህል ተገቢ ነው?
በዚህ ጉዳይ አል ዐይን አማርኛ ባለሙያ አነጋግሯል።የህግ መምህር እና ጠበቃ ዘመድኩን መካሻ ለረጅም አመታት የታክስ ህግን ሳስተምር መሰል አሰራር አላጋጠመኝም ያላሉ፡፡
“አሰራሩ በታክስ ስርአቱም ውስጥ ሆነ በአገልግሎት ክፍያ ውስጥ አልተካተተም በመሆኑም አንድ ንብረት ከሀገር ውስጥ ሲወጣም ሆነ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ተገቢውን የቀረጥ ክፍያ ከከፈለ ለንብረቱ ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍል አይገደድም” ሲሉ አቶ ዘመድኩን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።
የኮቴ ክፍያ የሚባል የአገልግሎት ክፍያ በመመሪያ እና በአዋጅ የወጣ አሰራር የለውም የሚሉት የህግ ባለሙያው ክፍያው የሚጠየቀው የአንድ የውጭ ሀገር ተሸከርካሪ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ እንደሆነ እርሱንም የፌደራል የጉምሩክ ተቋማት ብቻ ከፍያውን እንደሚያስከፍሉ ነግረውናል፡፡
አክለውም ክፍያው የአገልግሎት ክፍያ ነው ቢባል እንኳን የፌደራል መንግስት በሰራቸው መንገዶች ላይ ክልሎች ክፍያ የመሰብሰብ የህግ መሰረት እንደሌላቸው ያነሳሉ፡፡
የገንዘብ አሰባሰቡ ህጋዊ የሆነ መመሪያ እና አሰራር ስለሌለው በኦዲት ውስጥ በተገቢው መንገድ ስለማለፉ አጠራጠራለሁ የሚሉት አቶ ዘመድኩን በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት ላልተገባ ጥቅም ማካበቻ በር እንደሚከፍት ሲከፋም በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ስጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ክፍያው ተገቢ ነው ተብሎ ከተወሰነ በምን ያህል ርቀት በየትኛው ኬላ ላይ ስንት ብር መከፈል እንዳለበት አስፈላጊው ህግ እና መመርያ ወጥቶለት የተሸከርካሪ ባለንብረቶች እና አሽከርካሪዎች እንዲያውቁት መደረግ አለበት ተብሏል፡፡
በዚህ ረገድ አሰራሩ ለህገወጥነት የተጋለጠ በመሆኑ የፌደራል እና የክልል መንግስታት ወጥ የሆነ አሰራር በመዘርጋት በኩል ህገ ወጦችም ላይ እርምጃ በመውሰድ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የህግ ባለሙያው መክረዋል።