በአዲስ አበባ በጣለ ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ የጎርፍ አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለፀ
የጎርፍ አደጋው በአስኮ፣ በአደይ አበባ፣ በጀርመን አደባባይና በጎልፍ ክለብ አካባቢዎች መድረሱን የከተማ አስተዳሩ አስታውቋል
በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን ወደ ህክምና መስጫ በማጓጓዝ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል
በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በጣለው በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ በሰዉ ሕይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት መድረሱን የከተማ አስተዳሩ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ ከሰዓት በኋላ አዲስ አበባ በጣለው በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ምክንያት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ መከሰቱን ገልፀዋል።
የጎርፍ አደጋው በአስኮ፣ በአደይ አበባ፣ በጀርመን አደባባይና በጎልፍ ክለብ አካባቢዎች መድረሱን እና በአደጋው እስከአሁን ድረስ መንገዶች የተዘጉ መሆናቸውን ማምሻውን ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በጎርፍ አደጋውም በሰዉ ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በመግጽ፤ በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውንም አስታውቀዋል።
በአደጋው በሰዉ ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የገለጹት ምትል ከንቲባዋ የአደጋውን መጠን ግን በግልጽ አላስታወቁም።
የድንገተኛና የእሳት አደጋ ሰራተኞቻችን በቦታዎቹ በመገኘት ሰብዓዊ ጉዳት እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የገለፁት ምክትል ከንቲባዋ ተጎጂዎችን ወደ ህክምና መስጫ በማጓጓዝ እና የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የብሄራዊ ሜትሮዎሎጂ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመጪዎቹ ቀናት ከፍተኛ መጠን ያለዉ የዝናብ ስርጭት ስለሚኖር ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንድታደርጉ ምክትል ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል ።