የኢራኑን ፕሬዝዳንት ያሳፈረች ሄሊኮፕተር ላይ "አደጋ" መድረሱ ተነገረ
የነግስ አድን ሰራተኞችም ሄሊኮፕተሯ በ”አደገኛ ሁኔታ” ወዳረፈችበት አካባቢ ማቅናታቸው ነው የተገለጸው
የነፍስ አድን ስራው በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ምክንያት እየተፈተነ ነው ተብሏል
የኢራኑን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲን ያሳፈረች ሄሊኮፕተር ላይ አደጋ መድረሱ ተነገረ።
የኢራን ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሄሊኮፕተሯ ያረፈችበት መንገድ “አደገኛ” መሆኑን ከመጥቀስ ውጭ የአደጋውን መንስኤ በዝርዝር አላቀረበም።
አደጋው ከአዘርባጃን ጋር በምትዋሰነውና ከቴህራን በ600 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጆልፋ በተሰኘች ከተማ መድረሱ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ከአዘርባጃን አቻቸው ኢልሃም አሊየቭ ጋር ሀገራቱ በአራስ ወንዝ የገነቡትን ግድብ ለመመረቅ ወደ አካባቢው ማምራታቸው ቀደም ብሎ ተዘግቧል።
ለምረቃው ሶስት ሄሊኮፕተሮች ባለስልጣናትን አሳፍረው መጓዛቸውና ሁለቱ በሰላም መመለሳቸውን የጠቆመው ታስኒም የዜና አገልግሎት፥ ሁለቱ በሰላም መመለሳቸውን ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ራይሲን ባሳፈረችው ሄሊኮፕተር ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሆሴን አሚራብዶላሂያን እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት አብረው ጉዞ ላይ ነበሩ ተብሏል።
እነዚህ ባለስልጣናት የድረሱልን ጥሪ ማስተላለፋቸውንም ነው ዘገባው የጠቀሰው።
የነፍስ አድን ሰራተኞች አደጋው ደርሶበታል ወደተባለው አካባቢ መድረሳቸውና ፍለጋው መቀጠሉን ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የወጡ ዘገባዎች አመላክተዋል።
ሄሊኮፕተሯ አርስፓራን በተባለ ጫካ ውስጥ እንደምትገኝ የጠቀሰው ፋርስ የዜና ወኪል፥ የነፍስ አድን ሰራተኞች አሰሳቸውን ቢቀጥሉም በአካባቢው ያለው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ፈታኝ ሆኗል ብሏል።
የኢራን ምክትል ፕሬዝዳንት አደጋው ወደደረሰበት አካባቢ ማምራታቸውና ኢራናውያን ፕሬዝዳንታቸውና ሌሎች ባለስልጣናት በአደጋው ጉዳት እንዳይደርስባቸው በመጸለይ ላይ መሆናቸውም ተዘግቧል። >