ሀገሪቱ ሳምንታዊ የስራ ሰዓትን ከ44 ወደ 40 ሰዓት ዝቅ አድርጋለች
ኢራን የሳምንቱ እረፍት ቀናትን ወደ አርብ እና ቅዳሜ አዞረች
ኢራን ላለፉት በርካታ ዓመታት ከቅዳሜ እስከ ረቡዕ ድረስ ያሉ ቀናት የስራ ቀናት አድርጋ ቆይታለች፡፡
ሐሙስ እና አርብ ደግሞ የሳምንቱ የእረፍት ቀናት አድርጋ ስትጠቀም የቆየችው ኢራን ይህንን አሰራር እንደቀየረች አስታውቃለች፡፡
የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት ባስተላለፈው አዲስ ትዕዛዝ መሰረትም የበኢራን ምድር የሳምንቱ እረፍት ቀናት ወደ አርብ እና ቅዳሜ እንዲቀየር ወስኗል፡፡
ከዚህ በፊት በነበረው የስራ ቀናት አማካኝነት ሰራተኞች በሳምንት መስራት የሚጠበቅባቸው ጊዜ 44 ሰዓታ የነበረ ሲሆን በአዲሱ ህግ መሰረት የስራ ሰዓት ጊዜ ወደ 40 ሰዓት ዝቅ ብሏል ተብሏል፡፡
እንደ አል አረቢያ ዘገባ ከሆነ ጉዳዩ በሀገሪቱ ዋነኛ መከራከሪያ አጀንዳ የነበረ ሲሆን የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤቱ ሰፊ ክርክር ካደረገ በኋላ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡
የሳምንታዊ እረፍት ቀናት የተቀየረው ከዚህ በፊት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ኢራን ከሌላው ዓለም በመለየት ዋነኛ የቢዝነስ ማንቀሳቀሻ ቀናት በሆነው ሐሙስ ስራ መዝጋቷ ኢኮኖሚውን እየጎዳው ነው በሚል የቀረበ አስተያየትን መነሻ በማድረግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ኢራን አርብ ዕለትን ቀኑን ሙሉ ዜጎች በጸሎት እና በእርፈት እንዲያሳልፉ ከፈቀዱ ጥቂት የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷናት፡፡
ይሁንና የተወሰኑ አክራሪ ኢራናዊያን ሀገሪቱ የሳምንታዊ እረፍት ቀናትን ወደ ቅዳሜ መውሰዷ የምዕራባዊን እና ክርስቲያን ዘመን አቆጣጠርን ከሚከተሉ ሀገራት ጋር ያመሳስላታል ሲሉ ተችተዋል፡፡