አሜሪካ ከኢራን ጋር በሶስተኛ ወገን በኩል እየተወያየች መሆኗ ተገለጸ
የሁለቱ ሀገራት ውይይት በመካከለኛው ምስራቅ የከፋ ቀውስ እንዳይፈጠር በሚል ነው ተብሏል
ሀገራቱ በሶስተኛ ወገን በኩል ካሳለፍነው ጥር ጀምሮ በመወያየት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል
አሜሪካ ከኢራን ጋር በሶስተኛ ወገን በኩል እየተወያየች መሆኗ ተገለጸ፡፡
በኢራን ላይ ተደጋጋሚ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን በመጣል የምትታወቀው አሜሪካ በሶስተኛ ወገን በኩል እየተወያየች ነው ተብሏል፡፡
አል አረቢያ አክሲስን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድር ከኢራን ባለስልጣናት ጋር በመወያየት ላይ ነው፡፡
አሜሪካ ከኢራን ጋር መወያየትን የመረጠችው በመካከለኛው ምስራቅ እየተከሰቱ ያሉ ቀውሶች እንዳይባባሱ እና ለመቆጣጠር እንዲቻል ነውም ተብሏል፡፡
በአሜሪካ በኩል የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መካከለኛው ምስራቅ አማካሪ ብሬት ማክጉርክ እና በኢራን የአሜሪካ አምባሳደር አብራም ፓሌይ ከኢራን ጋር እየተደራደሩ ናቸው የተባለ ሲሆን በኢራን በኩል ግን እስካሁን የተደራዳሪዎቹ ማንነት አልተጠቀሰም፡፡
እንዲሁም አሜሪካ እና ኢራን በሶስተኛ ወገን እንዲደራደሩ እያደረገ ያለው አካልም ያልተጠቀሰ ሲሆን ውይይቱ ካሳለፍነው ጥር ወር ጀምሮ በመካሄድ ላይ ተገልጿል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ውይይት በተለይም የኢራን እና እስራኤል የቀጥታ ግጭት ውስጥ ከገቡበት ሚያዚያ ወር ወዲህ የበለጠ እየተደጋገመ እና እየጠነከረ እንደመጣም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ኢራን የሳምንቱ እረፍት ቀናትን ወደ አርብ እና ቅዳሜ አዞረች
ባሳለፍነው ጥቅምት ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የእስራኤል እና ኢራን ግንኙነት የበለጠ እየሻከረ መጥቷል፡፡
አሜሪካ በእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ውስጥ ጣልቃ እንዳትገባ ኢራን ብታስጠነቅቅም ዋሸንግተን በግልጽ ለእስራኤል ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች፡፡
ይህን ተከትሎ አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያሏት ወታደራዊ ማዘዣዎች በኢራን ይደገፋሉ በሚባሉ ታጣቂዎች የጥቃት ኢላማ ሆነዋል፡፡
በተለይም በጆርዳን፣ ኢራቅ እና ሶሪያ ያሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ማዘዣዎች የተለያዩ ጥቃቶችን ያስተናገዱ ሲሆን ሶስት የዋሸንግተን ወታደሮች ተገድለዋል፡፡