ቲዬሪ ሄንሪ “ሊቨርፑል የኃያልነት ዘመኑ እያከተመ ነው” አለ
ሄንሪ ይህን ያለው ሊቨርፑል ትናንት በስፔኑ ሪያል ማድሪድ የደረሰበትን 5ለ2 ሽነፈት ተከትሎ ነው
ሄንሪ፤ “አንዳንድ ተጫዋቾች ለሊቨርፑል የመጫወት ደረጃ ላይ አይደሉም” ሲል ተናግረዋል
ፈረንሳዊው የቀድሞ የአርሰናል አጥቂ ቲዬሪ ሄንሪ “ ሊቨርፑል የኃያልነት ዘመኑ እያከተመ ነው” ሲል ተናገረ።
ሄንሪ ይህን ያለው ላላፉት ዓመታት በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እንዲሁም ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ኃያልንቱን ማሳየት የቻለው ሊቨርፑል ትናንት በስፔኑ ሪያል ማድሪድ የደረሰበትን 5 ለ2 ሽነፈት ተከትሎ ነው።
የሊቭረፑል የወቅቱ አቋም ደካማ የሚባል መሆኑ በርካቶች የሚያነሱት ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል።
“ክለቡ መሰረታዊ ለውጥ ያስፈልገዋል” ያለው ቲዬሪ ሄንሪ፤ አሁን ባለው የቡድን ስብስብም ሆነ ብቃት ከቀጠለ አሁን ከቻምፒዮንስ ሊጉ መሰናበት ብቻ ሳይሆን በቀጣዩ አመት በአውሮፓ መድረክ ላናየው እንችላለን ሲለም ያለውን ስጋት ገልጿል።
“ሊቨርፑል የኃያልነት ዘመኑ መጨረሻ ላይ ነው፤ አንድ ነገር መለወጥ አለበት" ነው ያለው ሄንሪ። ፈረንሳዊው ኮከብ ይህን ሲል ጀርመናዊው አስልጣኝ ጀርገን ክሎፕ መሰናበት አለባቸው ማለቱ እንዳልሆነም ተናግሯል።
ሄንሪ "ክሎፕ መሄድ ያለበት አይመስለኝም፤ ነገር ግን አንዳንድ ተጫዋቾች ለሊቨርፑል የመጫወት ደረጃ ላይ አይደሉም" ማለቱም ነው ስካይ ስፖርት የዘገበው።
እንደ ሄንሪ ሁሉ በትናንትናው የሊቭረፑል አቋም መበሳጨቱን የገለጸው ደግሞ የቀድሞ የሊቭረፑል አንጋፋ ተጨዋች ጄሚ ካራገር ነው።
በትናንትናው የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ደካማ ሊቨርፑል መመልከቱን የገለጸው ካራገር፤ በተለይም የቡድኑ ተከላካይ ክፍል ወቅሷል።“ተከላካይ ክፍሉ ፍጹም ያልተረጋጋ ነበር” ሲልም ነው የተናገረው።
"ይህ የሊቨርፑል ተከላካይ ክፍል ሲነገረን እንደነበረው የምርጥ ተጨዋቾች ስብስብ አይደለም ፤ መቋቋም አልቻለም ሊቨርፑል ለዓመታት ይታወቅበት ከነበረው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል እጅግ የተለየና ደካማ ነው” ሲልም አክሏል።