“የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተወዳጁ የዓለማችን ሊግ ነው” ሲል የኢንተር ሚላኑ አሰልጣኝ ሲሞኒ ኢንዛጊ ተናገረ
የሮናልዶ ከጁቬንቱስ መልቀቅ ክለቡን እንደማይጎዳውም ነው ኢንዛጊ የተናገረው
ኢንዛጊ የሊቨርፑሉ የፊት መስመር ተጫዋች ሳላህ ኢንተርን እንዲቀላቀል ይፈልጋል
“የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተወዳጁ የዓለማችን ሊግ ነው” ሲል የኢንተር ሚላኑ አሰልጣኝ ሲሞኒ ኢንዛጊ ተናገረ።
የቀድሞው የጣልያን ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ሲሞኒ ኢንዛጊ እንዳለው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓለማችን ጠንካራ ውድድር የሚካሄድበት ተወዳጅ ሊግ ነው።
ኢንዛጊ ከአል ዐይን ስፖርት ኒውስ ጋር ባደረገው ቆይታ የስፔን ፕሪሜራ ሊጋ ሜሲን በመልቀቁ ምክንያት በጣልያን መበለጡን ተናግሯል።
በጨዋታ ጥራት፣ ፉክክር እና በሌሎች እግር ኳሳዊ ምከንያቶች በዓለማችን ካሉ የእግር ኳስ ውድድሮች መካከል የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ያለውን ተወዳጅነት ገልጿል ኢንዛጊ፡፡
የጣልያን ሴሪ ኤ ደግሞ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተናገረም ሲሆን የስፔን ሊግ ተወዳጅ ተጨዋቾች በየጊዜው መልቀቃቸው ሊጉን እንደጎዳው ጠቁሟል።
የኢንተር ሚላን ክለብ ተጫዋች የነበሩት ሞሮኳዊው ሀኪም ዚያች እና ቤልጂየማዊው ሮሜሮ ሉካኩ መልቀቅ እንደሚቆጭም ነው የገለጸው።
የሊቨርፑሉን የፊት መስመር ተጫዋች ግብጻዊውን ሞሀመድ ሳላህን አደንቃለሁ ያለም ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር ያለው ኮንትራት በዚህ ዓመት ስለሚጠናቀቅ ውሉን ከማራዘሙ በፊት እንዲያስብበት ሲልም ሳላህ ኢንተርን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርቧል።
ጁቬንቱስን ለቆ ከ12 ዓመት በኋላ ማንችስተርን የተቀላቀለው ፖርቹጋላዊው ክርሲቲያኖ ሮናልዶ ጁቬንቱስን እንደማይጎዳውም ኢንዛጊ ተናግሯል።
“ጁቬንቱስ ታላቅ ክለብ ነው አንድ ተጫዋቹን ስላጣ የከፋ የውጤት ማሽቆልቆል አያጋጥመውም” ሲልም ነው ያስቀመጠው፡፡
ሜሲ ለ17 ዓመታት ከነበረበት የልጅነት ክለቡ መልቀቁ ያልተጠበቀ ነበር ያለው የኢንተርሚላኑ አጥቂ ኢንዛጊ ባርሴሎና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የገንዘብ ቀውስ ስለገጠመው ሜሲ ለመልቀቅ መገደዱንም ተናግሯል።
ሌላኛው አሰልጣኙ ከአል ዐይን ስፖርት ጋር በነበረው ቃለመጠይቅ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የጆሴ ሞሪንሆ ወደ ሮማ መምጣት አንዱ ነበር።
“ሞሪንሆ በጣም ጎበዝ አሰልጣኝ ነው፤ ከኢንተር ጋር ጥሩ እና ስኬታማ ጊዜዎችን አሳልፏል ለጣልያን እግር ኳስ አዲስ ባለመሆናቸው በቀላሉ ይላመዳሉ ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ተናግሯል።