የሊቨርፑል ያለመሸነፍ ተስፋ ትናንት ምሽት በዋትፎርድ ተገታ
የሊቨርፑል ያለመሸነፍ ተስፋ ትናንት ምሽት በዋትፎርድ ተገታ
ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ ያለምንም መሸነፍ ሲገሰግስ የነበረው ሊቨርፑል ትናንት ምሽት በዋትፎርድ 3 ለ 0 በመሸነፍ እጁን ሰጥቷል፡፡
ዋትፎርዶች ከመጀመሪያው እስከመጠናቀቂያው ምርጥ በነበሩበት የቪካሬጅ ሮድ ጨዋታ ኢስማኢላ ሳር 2 ግቦችን ሲያስቆጥር አምበሉ ትሮይ ዴኒ ሶስተኛዋን አክሏል፡፡
ሊቨርፑል የምሽቱን ጨዋታ አሸንፎ ታሪክ እንደሚሰራ የብዙዎች እምነት ነበር፡፡ ምክኒያቱም 18 ተከታታይ የሊጉን ጨዋታዎች ያሸነፉት ሊቨርፑሎች የማታውን ጨዋታ ቢያሸንፉ ክብረ-ወሰን ይይዙ ነበር፡፡
ባለፈው ሳምንት ከዌስትሃም ጋር በነበራቸውም ጨዋታ ክፉኛ የተፈተኑት ሊቨርፑሎች የማታ ማታ በጭንቀት አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል፡፡ በምሽቱ ጨዋታም ሊቨርፑል ኢላማውን የጠበቀ 1 ኳስ ብቻ ነው የሞከረው፡፡
የሊቨርፑል መሸነፍ ግን ክለቡ ለዋንጫ የሚያደርገውን ጉዞ የሚገታው አይደለም፡፡ በ22 ነጥብ ልዩነት ሊጉን የሚመራው ክለቡ ዓመቱን ያለሽንፈት እንደሚያሸንፍና አዲስ ታሪክ እንደሚያስመዘግብ ይጠበቅ በነበረበት ወቅት ነው ሽንፈትን ያስተናገደው፡፡
ዋትፎርድ የምሽቱን ጨዋታ በማሸነፍ ከወራጅ ቀጣና በአንድ ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡
በሊጉ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቼልሲም ምሽት በቦርንማውዝ ሜዳ ያደረገውን ጨዋታ 2 አቻ በመለያየት ነጥብ ጥሏል፡፡ ይሄም የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለማረጋገጥ ለአራተኛ ደረጃ ለሚፎካከሩት ከስሩ የሚገኙ ክለቦች መልካም አጋጣሚን የፈጠረ ነው፡፡
ዛሬ ማንችስተር ዩናይትድ ወደ ጉዲሰን ፓርክ አቅንቶ ከኤቨርተን እንዲሁም ቶተንሃም ከ ዎልቭስ በሜዳው በተማሳሳይ 11 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፡-ሮይተርስ