ፈንጅ አነፍናፊው አይጥ ‘ማጋዋ’ ከ5 የአገልግሎት ዓመታት በኋላ ጡረታ ወጣ
የ20 የእግር ኳስ ሜዳ ያህል ስፋት ያለውን 141 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ በማነፍነፍ የተዋጣለት ተግባር መፈጸሙም ነው የተነገረለት
ማጋዋ ያለፉትን 5 ዓመታት ያልመከኑ 71 ፈንጆችን አነፍንፏል
ያለፉትን 5 ዓመታት ያልመከኑ ፈንጆችን በማነፍነፍ ሲያገለግል የነበረው ማጋዋ የተሰኘው አይጥ ጡረታ ወጣ፡፡
ማጋዋ በምህጻረ ቃሉ APOPO በሚባል የቤልጂዬም የግል ፈንጅ አምካኝ ድርጅት ሰልጥኖ ያለፉትን 5 ዓመታት የተዋጣለት ተግባር መፈጸሙ ተገልጿል፡፡
እንደ ድርጅቱ ገለጻ ከሆነ ማጋዋ የ20 የእግር ኳስ ሜዳ ያህል ስፋት ያለውን 141 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ በማነፍነፍ 71 ፈንጂዎችን እና 38 ያልተፈነዱ ሌሎች ጦር መሳሪያዎችን እንዲመክኑ ለማድረግ ችሏል፡፡
በዚህ የጀብድ ተግባሩ ከእንግሊዝ ሳይቀር የተለያዩ የሜዳይ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡
APOPO 8 ያህል ዓመታትን የመኖር ተፈጥሮ አላቸው ያለላቸው ማጋዋን መሰል አፍሪካዊ ዝርያ ያላቸው አይጦች በእንዲህ ዓይነት ተግባራት ላይ የተሻሉ ግልጋሎቶችን ለመስጠት እንደሚችሉ ገልጿል፡፡
ማጋዋ ለዚሁ ተግባር ተብለው በድርጅቱ ከሰለጠኑ አይጦች መካከል ነው፡፡ በአካላዊ ይዞታውም ከሌሎች አይጦች የተሻለ ነው፡፡
ፈንጂና ሌሎችንም ተቀጣጣይ የጦር መሳሪያ ቅሪቶች አነፍንፎ ጥቆማ መስጠት እንዲችል ሆኖ ሰልጥኗል፡፡
በዚህም የተዋጣለት ተግባርን ለመፈጸም ችሏል ያለው ድርጅቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ያለምንም ስጋት ወጥቶ መግባት እና መኖር፤ መስራትም እንዲችሉ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2014 በታንዛኒያ የተወለደ ሲሆን በ2016 ሴም ሪፕ ወደ ተሰኘችው የሰሜናዊ ካምቦዲያ ከተማ ተወስዶ በአንግኮር ቤተ መቅደሶች የማነፍነፍ ተግባሩን መጀመሩን የአሶሼትድ ፕሬስ እና ሲኤንኤን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
በካምቦዲያ በቬትናም ጦርነት ጊዜ ተቀብረው የቀሩ በርካታ የጦር ቅሪቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡
ድርጅቱ በተለያዩ የጦርነት እና የግጭት ጊዜያት የተቀበሩ ፈንጂዎችን ለማምከን አንጎላ፣ ዚምባብዌ እና ሞዛምቢክን ጨምሮ በተለያዩ 59 የዓለማችን ሃገራት ተሰማርቶ ይገኛል፡፡
በእነዚህ 59 ሃገራት 60 ሚሊዬን ገደማ ሰዎችን ስጋት ላይ የጣሉ እና እስካሁን ያልመከኑ ፈንጂዎች እንዳሉ ነው የሚያስታውቀው፡፡
በፈንጂዎች እና በሌሎች ጦር መሳሪያዎች ቅሪቶች ሳቢያ በ2018 ብቻ የ6,897 ሰዎች ህይወት ማለፉንም ይገልጻል፡፡