የሄዝቦላ መሪ ከፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች አመራሮች ጋር ድል በማድረግ ጉዳይ መከረ
በሊባኖስ፣ ሶሪያ እና በየመን ያሉ ታጣቂዎች እንዲሁም ኢራን ከእስራኤል ጋር ለገጠመው ሀማስ አጋርነታቸውን አሳይተዋል
የጦር መርከቦቿን ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ ያስጠጋችውን አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት ደግሞ ከእስራኤል ጎን ተሰልፈዋል
የሊባኖሱ የሄዝቦላ መሪ ከፍልስጤም ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተገናኝቶ "ድል በማድረግ" ጉዳይ ተወያይቷል።
መሪው ከፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች ጋር መገናኘቱን ሮይተርስ የሄዝባላውን አል-ማናር ቴሌቪዥን ጠቅሶ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖቹ ሀማስ እና እስላማዊ ጅሃድ ከሄዝቦላ መሪ ጋር በተገናኙበት ወቅት በጋዛ ያለውን ትግል በድል ለማጠናቀቅ ጥምረታቸው ምን መሆን እንዳለበት ተወያይተዋል።
ስብሰባውን የሄዝቦላው ሰይድ ሀሰን ነስረላህ፣ የሀማስ ምክትል ኃላፊ ሳላህ አል አሮሪ እና የእስላማዊ ጅሃድ ኃላፊ ዛይድ አል ናቅሃላ ማካሄዳቸውን አል ማናር በዘገባው ገልጿል።
"በስብሰባው...በአለም አቀፍ ደረጃ የተያዘውን አቋም በመገምገም፣ ትግሉ ምን መምሰል አለበት" በሚለው ጉዳይ ምክክር መደረጉን ይኸው ሚዲያ ዘግቧል።
በሊባኖስ፣ ሶሪያ እና በየመን ያሉ ታጣቂዎች እንዲሁም ኢራን ከእስራኤል ጋር ለገጠመው ሀማስ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በሰሜን እስራኤል በኩል ጥቃት በመክፈት ለሀማስ ያለውን አጋርነት በተግባር በማሳየት ግንባር ቀደም ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት እስራኤል በዌስት ባንክ፣ በጋዛ እና በሰሜን እስራኤል በኩል እየተዋጋች ትገኛለች።
ሀሉት ግዙፍ የጦር መርከቦቿን ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ ያስጠጋችውን አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን ሀገራት ደግሞ ከእስራኤል ጎን ተሰልፈዋል።
ሩሲያ እና የአረብ ሀገራት ተኩስ አቁም እንዲደረግ ቢወተውቱም፣ እነአሜሪካ ትኩረታቸውን ሰብአዊ እርዳታ ማድረስ ላይ ብቻ አተኩረዋል።