ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጀች መሆኗን የካሚኒ አማካሪ ተናገሩ
ኢራን በእስራኤል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥተኛ ጥቃት የፈጸመችው የሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ በቴህራን ከተገደለ በኋላ ነው
ኢራን በእስራኤል ላይ 200 ገደማ ሚሳይሎችን ካዘነበች ከሶስት ሳምንታት በኋላ የእስራኤል ተዋጊ ጄቶች በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ በሶስት ዙር ጥቃት ፈጽመዋል
ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጀች መሆኗን የካሚኒ አማካሪ ተናገሩ።
ኢራን እስራኤል ለፈጸመችባት ጥቃት ምላሽ ለመስጠት እየተዘጋጀች መሆኗን የሀገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ አማካሪ ቅዳሜ እለት ለታተመው የኢራኑ ታስኒም ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
ባለፈው ጥቅምት 26 ኢራን በእስራኤል ላይ 200 ገደማ ሚሳይሎችን ካዘነበች ከሶስት ሳምንታት በኋላ የእስራኤል ተዋጊ ጀቶች በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ በሶስት ዙር ጥቃት ፈጽመዋል።
ኢራን በእስራኤል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥተኛ ጥቃት የፈጸመችው የሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ በቴህራን ከተገደለ በኋላ ነው።
እስራኤል ለዚህ ግድያ ኃላፊነት ባትወስድም፣ ኢራን እና ሀማስ ግን ግድያውን የፈጸመችው እስራኤል ነች ብለው ያምናሉ።
እስራኤል ኢራን ለፈጸመችባት የመጀመሪያ ቀጥተኛ ጥቃት፣ ምላሽ ሰጥታ ነበር።ነገርግን የሁለቱ ሀገራት ጥቃት መመላለስ ለሁለተኛ ጊዜ ተደግሟል።
የአንድ አመት ያህል በጋዛ በሀማስ ላይ መጠነሰፊ ጥቃት ስታደርስ የነበረችው እስራኤል ፊቷን በሊባኖስ ወደሚንቀሳቀሰው የኢራን የቀጣናው ዋነኛ አጋር ወደ ሆነው ሄዝቦላ አዞረች።
እስራኤል "በንከር በስተር" የተባለውን አሜሪካ ሰራሽ ቦምብ በመጠቀም በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ደቡብዊ ዳርቻ በፈጸመችው ካባድ እና ተከታታይ የአየር ጥቃት የሄዝቦላን መሪ ሀሰን ነስረላህን ጨምሮ በርካታ የቡድኑ መሪዎች ተገደሉ። እስራኤል የአየር ጥቃት ካደረገች በኋላ በሊባኖስ ላይ በምድር በእግረኛ ጦር ወረራ ፈጸመች።
ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳይል ናዳ ያዘነበችው በዚህ የእስራኤል እርምጃ በመቆጣት ነበር።
እስራኤል የኢራን የሚሳይል ጥቃት በሰጠችው ምላሽ ሶስት ዙር በኢራን ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።
አሁን ላይ ኢራን ለዚህ ጥቃት ነው ምላሽ ለመስጠት እየተወጋጀች መሆኗን የገለጸችው።