ሩሲያ በዩክሬን ላይ ድል አላስመዘገበም ያለችውን የጦር አዛዥ ከሀላፊነት አነሳች
በምስራቃዊ ዩክሬን በኩል ያለው የሩሲያ ጦር አዛዥ በቂ ድል አላስመዘገበም በሚል ከሀላፊነት ተነስቷል
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንድ ሺህ ቀን አልፎታል
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ድል አላስመዘገበም ያለችውን የጦር አዛዥ ከሀላፊነት አነሳች፡፡
ለሁለት ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት አንድ ሺህ ቀን ያለፈው ሲሆን ጦርነቱ በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ይገኛል፡፡
ሩሲያ ወደ ዩክሬን የላከችው ጦር ከመቼውም ጊዜ በላይ ብዙ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ ሲሆን በምስራቅ ዩክሬን በኩል ያለው ጦር ግን በቂ ድል እያስመዘገበ አይደለም የሚል ትችት ቀርቦበታል፡፡
ሮይተርስ ለሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ቅርብ የሆኑ ጸሃፊዎችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ በምስራቃዊ ዩክሬን ግምባር ሲቨርስክ በኩል ያለው የጦር አዛዥ ከሀላፊነት ተነስቷል፡፡
ኮለኔል ጀነራል ጌናዲ አናሽኪን የተሰኘው ኮማንድር ከሀላፊነት የተነሳው ጀነራሉ የሚመራው ጦር እያስመዘገበ ያለው ድል አነስተኛ ነው በሚል ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አዛዡ ሀሰተኛ ሪፖርት ልኳል የተባለ ሲሆን ይህም ከሀላፊነት ለመነሳቱ ሌላኛው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
ሲቨርስክ በተሰኘው የውጊያ ግምባር ያለው ይህ ጦር የዩክሬኗን ክራማቶርስክ የተሰኘችውን ቁልፍ ከተማ እንዲቆጣጠር ተልዕኮ ቢሰጠውም ይህን አላደረገም የሚሉ ትችቶች ሲቀርቡበት እንደነበርም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ሩሲያ በምስራቃዊ የውጊያ ግምባሮች የሩሲያን ጦር ግስጋሴ ለመመከት የኔቶ አባል ሀገራት ስሪት የሆኑ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎችን ጭምር በመጠቀም ላይ ትገኛለች፡፡
ሩሲያም ለዚህ ምላሽ በሚል ኦሬሽኒክ የተሰኘ አዲስ አህጉራ አቋራጭ ሚሳኤል ወደ ዩክሬኗ ቁልፍ የጦር መሳሪያ መጋዝን ድንፒሮ መተኮሷ ይታወሳል፡፡
የሁለቱ ሀገራት አዲሱ የረጅም ርቀት ሚሳኤል የጣገዘ ውጊያ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት እንዲቀሰቀስ መነሻ ሊሆን እንደሚችል እየተገለጸ ይገኛል፡፡