ሄዝቦላህ አሜሪካ ባቀረበችው የተኩስ አቁም ሃሳብ መስማማቱ ተነገረ
የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሊባኖስ ማብራሪያ በጠየቀችበት የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ዙሪያ ለመምከር ቤሩት ገብተዋል
እስራኤል በአጋሯ የቀረበውን የተኩስ አቁም ሃሳብ መቀበሏ ቢገለጽም በቤሩት የአየር ጥቃቷን ቀጥላለች
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ያቀረበችውን ረቂቅ የተኩስ አቁም ሃሳብ መቀበሉ ተነገረ።
ሄዝቦላህ በሊባኖስ የአሜሪካ አምባሳደር ሊዛ ጆንሰን ለሊባኖስ ፓርላማ አፈጉባኤ ናቢህ ቤሪ ያቀረቡትን ረቂቅ የተኩስ አቁም ሰነድ መመልከቱንና እሁድ ምሽት የአዎንታ ምላሽ መስጠቱ ነው የተገለጸው።
የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ ማካቲ ከአል አረቢያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ በረቂቁ ዙሪያ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ቢኖሩም በአብዛኛው የተስማማንበት ነው ብለዋል።
የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ አሞስ ሆችስቴንም ዛሬ ቤሩት የገቡ ሲሆን ማብራሪያ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ዙሪያ የፊት ለፊት ምክክር እንደሚያደርጉ ሬውተርስ ዘግቧል።
እስራኤልም በአጋሯ በኩል የቀረበውን የተኩስ አቁም ሃሳብ እንደምትቀበለው ቢነገርም የእስራኤል ጄቶች በቤሩትና አካባቢው የሚፈጽሙት ድብደባ ተጠናክሯል። ሄዝቦላህም ወደ እስራኤል ሮኬቶችን መተኮሱን ቀጥሏል።
እስራኤል ትናንት በቤሩት በፈጸመችው ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸውንና ከ30 በላይ መቁሰላቸውን የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
ሄዝቦላህም ትናንት ምሽት ወደ ቴል አቪቭ ሮኬቶችን በመተኮሱ ምክንያት መዲናዋ በማስጠንቀቂያ ደወል ድምጽ ተረብሻ አምሽታለች ነው የተባለው።
ተመቶ የወደቀ ሚሳኤልም በስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የእስራኤል ጦር ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
የሄዝቦላህ ሮኬት በሰሜናዊ እስራኤል ሽፋ አምር ከተማ የሚገኝ ህንጻን መትቶ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንም ገልጿል።
በስምንት ሳምንታት ውስጥ ከ1 ሚሊየን በላይ ሊባኖሳውያንን ከቀያቸው ያፈናቀለው የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት እንዲቆም በአሜሪካ አደራዳሪነት የተጀመረው ጥረት ተስፋ ሰጪ ስለመሆኑ በስፋት እየተዘገበ ነው።
የተኩስ አቁም ድርድሩ የ2006ቱን የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት ባስቆመው የመንግስታቱ ድርጅት የውሳኔ ሃሳብ 1701 ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ተጠይቋል። የውሳኔ ሃሳቡ ሄዝቦላህ ከእስራኣኤል ሰሜናዊ ድንበር በ20 ኪሎሜትሮች እንዲርቅ የሚጠይቅ ነበር።
የሊባኖሱ ቡድን እንዲደራደሩ እውቅና ለሰጣቸው የፓርላማ አፈጉባኤው ናቢህ ቤሪ የላከው ምላሽም ለጸጥታው ምክርቤት የውሳኔ ሃሳብ ተገዥ መሆኑን ያመላከተ ነው ተብሏል።