ሄዝቦላህ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ከ100 በላይ የእስራኤል ወታሮችን ገድያለሁ አለ
የእስራኤል ወታሮች በሊባኖስ ውስጥ በውጊያ ላይና በሰሜናዊ እስራኤል በተፈጸመ ጥቃት ነው የተገደሉት
የእስራኤል ጦር አንድም የሊባኖስን መንደር መቆጣጠር እንዳልቻለ ሄዝቦላህ አስታውቋል
የሊባኖሱ ቡድን ሄዝቦላህ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ብቻ ከ100 በላይ የእስራኤል ወታሮችነ መግደሉን አስታወቀ።
ሄዝቦላህ ባሳለፍነው ማክሰኞ ባወጣው መረጃ ተዋጊዎቹ ባሳለፍነው አንድ ወር ብቻ ከ100 በላይ የእስራኤ ጦር አባላትን መግደላቸውን ይፋ አድርጓል።
ወታሮቹ የት እና በየትኛው ቀን የሚለውን በዝርዝር ባያስቀምጥም፤ የእስራኤል ወታሮች የተገደሉት በሊባኖስ ውስጥ በውጊያ ላይና በሰሜናው እስራኤል በተፈጸመ ጥቃት መሆኑን ገልጿል።
እስራኤል በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የተወሰኑ መታሮቿ እንደተገደሉባት ታረጋግጥም፤ ሄዝቦላህ በጠቀሰው አሃዝ ላይ ግን አስተያየት አልሰጠችም።
እስራኤል እና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ወደ ግጭት ያመሩት የእስራኤል ጋዛ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን፤ የፊትለፊት ውጊያ ከጀመሩ ደግሞ ከ45 ቀናት በላይ ተቆጥረዋል።
ሄዝቦላህ ትናነት በሰጠው መግለጫው፤ የምድር ላይ የፊት ለፊት ውጊያ ከተጀመረበት እለት አንስቶ ተዋጊዎቹ የእስራኤል ጦር ከበርካታ የሊባስ ከተሞች አንዲያፈገፍግ አድርገዋል ብሏል።
ሂዝቦላህ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫውም የእስራኤል ጦር በ45 ቀናት በቆየው ጦርነት ውስጥ እንድ መንደር እንኳን መቆጣጠር አልቻለም ማለቱ ይታወሳል።
የሂዝቦላህ ቃል አቀባይ የሆኑት ሞሀመድ አፊፍ በደቡባዊ ሊባኖስ በሰጡት መግለጫ እስራኤል ጦሯን ወደ ሊባኖስ ብትልክም እስካሁን የያዘችው ቦታ የለም ሲሉ ተናግረዋል።
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳር በበኩላቸው፤ ሂዝቦላህን ከእስራኤል ድንበር አባረናል፣ ከእንግዲህ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ መታጠቅ አይችልም ማለታቸውም ይታወሳል።
እስራኤል እና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ወደ ግጭት ያመሩት የእስራኤል ጋዛ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን፤ ካሳለፍነው መስከረም ወር ወዲህ ደግሞ ወደ ለየለት ጦርነት ገብተዋል።
እስራኤል ሀሰን ነስረላህን ጨምሮ ከፍተኛ የሄዝቦላህ አመራሮችን የገደለች ሲሆን፤ ቤሩትን ጨምሮ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ በርካታ ከተሞችን በአየር ድብደባ አውድማለች።
በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የተገደሉ ሊባኖሳውያን ቁጥር 3 ሺህ 287 የደረሰ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ እዛኞቹ ባለፉት ሰባት ሳመንታት ውስጥ የተገደሉ መሆኑን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ሄዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል እና በእስራኤል ይዞታ ስር በሚገኙ የጎላን ተራች ላይ በፈጸመው ጥቃት ከ100 በላይ እስራኤላውያን መሞታቸው ተነግሯል።