አሜሪካ የሊባኖስን ጦርነት ለማስቆም የ60 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረስ እየሰራች ነው ተባለ
በስምምነት ሀሳቡ የሊባኖስ ደቡባዊ ድንበር ከጦር ቀጠና ውጪ በሰላም አስከባሪ ሀይሎች ሙሉ ቁጥጥር ስር ይዋል የሚለው ተካቷል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ልኡክ አሞስ ሆይስተን እና ሌሎች ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በነገው ዕለት ወደ ቴልአቪቭ ያቀናሉ
አሜሪካ የወከለቻቸው አሸማጋዮች በእስራኤል እና በሊባኖሱ ታጠቂ ሃይል ሄዝቦላህ መካከል ያለውን ጦርነት ለማስቆም በቀረበው ሀሳብ ዙርያ እየሰሩ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡
አደራዳሪዎቹ በሁለቱ ተዋጊዎች መካከል የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እየሰሩ ቢሆንም፤ እስራኤል በምስራቃዊ ሊባኖስ የባልቤክ ከተማ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው ለቀው እንዲወጡ በዛሬው እለት ትዕዛዝ አስተላልፋለች፡፡
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ከተነገሩ በኋላ በምስራቁ ክፍል የተሰማው ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያን ተከትሎ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከአካባቢው ለመውጣት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡
የሊባኖስ ሲቪል መከላከያ የክልል ኃላፊ ቢላል ራአድ፥ የእስራኤል ወታደራዊ አባል መሆኑን ከሚገልጽ ሰው የስልክ ጥሪ ከደረሰን በኋላ ነዋሪዎቹ ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ በሜጋፎን ጥሪ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
ለሶስተኛ ተከታታይ ቀን ሄዝቦላህ በደቡባዊዋ የሊባኖስ ከተማ ኪያም ከእስራኤል ጦር ጋር ከፍተኛ ውጊያ መደረጉን ገልጿል፡፡
ይህም ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የእስራኤል ወታደሮች ወደ ሊባኖስ ዘልቀው መግባታቸውን የሚያመላክት መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ባለፉት አምስት ሳምንታት ተፋፍሞ የቀጠለውን የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ጦርነት ለማስቆም እንዲሁም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ አለምአቀፋዊ ጥረቶች ቀጥለዋል፡፡
ሮይተርስ ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ እንደዘገበው የ60 ቀናቱ የተኩስ አቁም በ2006 ይፋ በተደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የውሳኔ ሀሳብ 1701 መሰረት ደቡባዊ ሊባኖስን ከጦር ቀጠና ነጻ በማድረግ በሰላም አስከባሪዎች ሙሉ ቁጥጥር ስር እንዲመለስ የሚጠይቅ ነው፡፡
ምንጮቹ የተመድ የውሳኔ ሀሳብ 1701 በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ባለፉት አምስት ሳምንታት በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ የቀጠለውን ጦርነት ለማቆም የውይይት መሰረት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም አዲሱ የተኩስ አቁም ስምምነት ከዚህ ቀደም በአሜሪካ እና ሌሎች አጋሮች ተግባራዊ እንዲደረግ ተጠይቆ የነበረውን የ21 ቀናት የተኩስ አቁም ሀሳብ የሚተካ ነው ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ልኡክ አሞስ ሆይስተን እና ሌሎች ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በነገው ዕለት ከእስራኤል መንግስት ጋር ለመምከር ወደ ቴልአቪቭ ያቀናሉ፡፡
ጦርነቱ በዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ በአፋጣኝ እንዲቋጭ እንፈልጋለን ያሉት በቤይሩት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ቃል አቀባይ ሳማ ሀቢብ ፤ የውሳኔ ሀሳብ 1701 ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ በድንበር አቅራቢያ የሚገኙ የሊባኖስ እና እስራኤል ዜጎች ወደ መኖሪያቸው የሚመልስ መፍትሄ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የእስራኤል ቻናል 12 ቴሌቪዥን ቴል አቪቭ የተመድ የውሳኔ ሀሳብ 1701 እስራኤል የጸጥታ ስጋት ከገጠማት ጣልቃ እንድትገባ በሚፈቅድ መልኩ እንዲሻሻል ትፈልጋለች ብሏል፡፡