ሊባኖስ ከእስራኤል ጋር ተኩስ አቁም ለማቆም የምታደርገውን ድርድር እደግፋለሁ - ኢራን
በሊባኖስ የአሜሪካ አምባሳደር ረቂቅ የተኩስ አቁም ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን፥ የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣንም በቤሩት ይገኛሉ
ቴህራን በ1982 የመሰረተችው ሄዝቦላህ እስራኤል ወረራዋን ካላቆመች የተኩስ አቁም ንግግር አይኖርም ማለቱ ይታወሳል
ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ከእስራኤል ጋር በምታደርገው ድርድር የምታሳልፈውን የትኛውንም ውሳኔ እንደምትደግፍ ኢራን አስታወቀች።
ሬውተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው በሊባኖስ የአሜሪካ አምባሳደር ሊዛ ጆንሰን ለሊባኖስ ፓርላማ አፈጉባኤ ናቢህ ቤሪ ረቂቅ የተኩስ አቁም ሰነድ አቅርበዋል።
አፈጉባኤው በተኩስ አቁም ድርድሮች ላይ እንዲሳተፉ በሄዝቦላህ ድጋፍ የተሰጣቸው ሲሆን በትናንትናው እለት ከኢራን ከፍተኛ ባለስልጣን አሊ ላሪጃኒ ጋር በቤሩት ተወያይተዋል።
በቤሩት የሚገኙት የአሜሪካን የተኩስ አቁም ጥረት ለማደናቀፍ ነው ወይ በሚል ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው የአያቶላህ አሊ ካሚኒ ልዩ አማካሪ፥ “ምንም አይነት ሻጥር የመስራት ፍላጎት የለንም፤ መፍትሄ ነው የምንፈልገው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“የሊባኖስ መንግስትን በየትኛውም አጋጣሚ እንደግፋለን፤ (የተኩስ አቁም ስምምነቱን) እያደናቀፈ የሚገኘው ኔታንያሁ እና የሚመራው ህዝብ ነው” ሲሉም አክለዋል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በፈረንጆቹ 1982 በኢራን አብዮታዊ ዘብ አማካኝነት መመስረቱና ከቴህራን የገንዘብና ትጥቅ ድጋፍ እንደሚያገኝ ይታወቃል።
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለፍልስጤማውያን አጋርነቴን ለማሳየት በሚል ወደ እስራኤል ሮኬት እና ሚሳኤሎችን መተኮሱ ከቴል አቪቭ ጋር ጦር አማዞታል።
በደቡባዊ ሊባኖስ በእግረኛ ጦር፤ በቤሩትና ሌሎች ከተሞች በአየር ድብደባ የቀጠለው የእስራኤልና ሄዝቦላህ ግጭት ከ2006ቱ ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ነው።
ሄዝቦላህ በአዲሱ መሪው ናይም ቃሲም በኩል እስራኤል ወረራዋን ካላቆመች ጦርነቱ ይቀጥላል፤ አቅማችን ገና አልተነካም ሲል ዝቶ በየእለቱ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ማስወንጨፉም በተኩስ አቁም ድርድሩ ላይ ጥላ አጥልቷል።
የእስራኤል የኢነርጂ ሚኒስትርና የደህንነት ካቢኔ አባሉ ኢሊ ኮህን ግን በአሁኑ ወቅት የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ከእስካሁኑ የተሻለ ተስፋ ሰጪ ነገር አለ ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ዋሽንግተን ፖስትም ኔታንያሁ አዲሱ የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋይትሃውስ ከመግባታቸው በፊት በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ጥድፊያ ላይ ናቸው ብሏል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ የ2006ቱን ጦርነት ባስቆመው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት የውሳኔ ሃሳብ መሰረት እንዲሆን እየተጠየቀ ነው።
የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 1701 ሄዝቦላህ ተዋጊዎቹንና የጦር መሳሪያዎቹን ከሊታኒ ባህር በስተሰሜን (ከእስራኤል ድንበር 20 ኪሎሜትር) እንዲያዘዋውር ያዛል።
ሄዝቦላህ የሊባኖስን ድንበር ጥሳ ከገባችው እስራኤል ጋር በዚህ ጉዳይ ይስማማል ተብሎ ባይጠበቅም አጋሩ ቴህራን ግን ተኩስ እስካስቆመ ድረስ የጸጥታው ምክርቤት የውሳኔ ሃሳብ ቢተገበር እንደምትደግፍ አስታውቃለች።
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ አማካሪ በቤሩት ምክክር ሲያደርጉ እስራኤል በመዲናዋ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በሚታይበት ታዩኔህ በተባለ አካባቢ ህንጻን ከመሬት ቀላቅላለች።
የእስራኤል ጦር የውጊያ ጄቶቹ የጦር መሳሪያ ማከማቻዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሄዝቦላህ መሰረተልማቶችን ማውደሙንና ንጹሃን እንዳይጎዱ አስቀድሞ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ማስተላለፉን ገልጿል።