“ድሉ የሀቀኛ ትግል አጋር ከሆነው አምላክ የተገኘ ነው” ብሏል ሄዝቦላህ
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ቡድን በእስራኤል ላይ ድል መቀዳጀቱን አወጀ።
ሄዝቦላህ በትናንታው እለት ከተደረሰው እና ተግባራዊ መደረግ ከጀመረው የተኩስ አቁም በኋላ ትናነት ምሽት የመጀመሪያውን መግለጫ አውጥቷል።
ሄዝቦላህ በመግለጫውም በእስራኤል ላይ ድል ማስመዝገቡን በማወጅ፤ “ድሉ የሀቀኛ ትግል አጋር ከሆነው አምላክ የተገኘ ነው” ብሏል።
ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ተዋጊዎቹ ዝግጁ መሆናቸውንም ቡድኑ አስታውቋል።
ሄዝቦላህ በመግለጫው አክሎም ተዋጊዎቹ “የጠላት እስራኤልን ምኞት እና ማንኛውንም ጥቃት ለመከላል በሙሉ ቁመናና ዝግጅት ላይ ናቸው” ብሏል።
ሄዝቦላህ እና እስራኤል በትናነትናው እለት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።
ለ60 ቀናት ይቆያል የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት የእስራኤል ወታደሮች ከሊባኖስ ለቀው እንዲወጡ እና የጸጥታ ማስከበር እና የድንበር ጥበቃውን የሀገሪቱ ጦር እንዲረከብ ያዛል።
ከዚህ ባለፈ የስምምነት ሰነዱ የጦር መሳርያ እንዲታጠቁ የተፈቀደላቸው አካላት የሊባኖስ ጦር፣ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሃይሎች፣ የመንግስት ደህንነት፣ የሊባኖስ ጉምሩክ እና የማዘጋጃ ቤት ፖሊሶች ብቻ ናቸው።
ከስምምነቱ በኋላ የሄዝቦላህ እጣ ፈንታ ምን ይሆን?
የሄዝቦላህ ከፍተኛ ባለስልጣን ሀሰን ፋድላላህ ከሊባኖሱ አልጀዲድ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ “ቡድኑ ከጦርነቱ በኋላ ተጠናክሮ ይወጣል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያንም ትግሉን ይቀላቀላሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ አክለውም ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር የጀመረው ጦርነት ካበቃ በኋላ ንቁ ሆኖ እንደሚቀጥል፣ የተፈናቀሉ ሊባኖሳውያን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በመርዳት እና በእስራኤል ጥቃት የወደሙትን አካባቢዎች መልሶ መገንባት ላይ እንደሚያተኩር ተናግረዋል።
“ነገር ግን የእስራኤልን ተስፋፊነት በመቃወም የሚደረገው ትግል እንደማይቋረጥ ላረጋግጥ እወዳለሁ” ነው ያሉት።
ስምምነቱ ተሳክቶ ወደ ዘላቂ የተኩስ አቁም የሚገባ ከሆነ ከሊባኖስ ጦር የተሻለ የተዋጊዎች ቁጥር እና የውግያ አቅም እንዳለው የሚነገርለት ሄዝቦላህ በቀደመው ልክ ከእስራኤል ጋር ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ እንደማይገባ ይጠበቃል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሀማስ እና ከኢራን ጋር የሚኖረው ግንኙነት ምን ሊመስል እንደሚችል በጥያቄ ውስጥ እንደሚገኝ ሮይተርስ አስነብቧል።
እስራኤል በሊባኖስ ባወጀችው ጦርነት የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ነስረላህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮችን ገድላለች።
ከዚህ ባለፈም ድንበር አቋርጣ በፈጸመችው የእግረኛ እና የአየር ጥቃት እስካሁን 3700 ንጹሀን ሲገደሉ 8.5 ቢሊየን የሚገመት ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አድርሳለች።