በስምምነቱ መሰረት ከመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በስተቀር ጦር መሳርያ መታጠቅ አይቻልም
ሄዝቦላህ እና እስራኤል በዛሬው እለት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ለ60 ቀናት ይቆያል የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት የእስራኤል ወታደሮች ከሊባኖስ ለቀው እንዲወጡ እና የጸጥታ ማስከበር እና የድንበር ጥበቃውን የሀገሪቱ ጦር እንዲረከብ ያዛል።
ተኩስ አቁሙ ዘላቂ የሰላም ስምምነትን ለማስፈጸም አላማው ያደረገ ሲሆን አሜሪካ የሊባኖስን ጦር የትጥቅ እና ወታደራዊ አቅም ለማጠናከር ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ግብታለች።
ከዚህ ባለፈ የስምምነት ሰነዱ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል ከሊባኖስ ወታደሮች እና የጸጥታ ሀይሎች ውጪ ትጥቅ መታጠቅን ከልክሏል።
ሮይተርስ ተመልክቸዋለሁ ያለውን የስምምነት ሰነድ ጠቅሶ እንደዘገበው የጦር መሳርያ እንዲታጠቁ የተፈቀደላቸው አካላት የሊባኖስ ጦር፣ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሃይሎች፣ የመንግስት ደህንነት፣ የሊባኖስ ጉምሩክ እና የማዘጋጃ ቤት ፖሊሶች ብቻ ናቸው።
ሁለቱም ወገኖች የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 1701ን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ይህም በሊባኖስ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የታጠቁ ቡድኖችን ትጥቅ ማስፈታት የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ጨምሮ የሚያካትት ነው።
በተጨማሪም ሄዝቦላህ በጦርነቱ የፈረሱበትን ወታደራዊ መሰረተ ልማቶች ድጋሚ እንዳይገነባ የሊባኖስ መንግስት በጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ እስራኤል ጠይቃለች።
ከስምምነቱ በኋላ የሄዝቦላህ እጣ ፈንታ ምን ይሆን?
ሄዝቦላህ በተኩስ አቁም ላይ እስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጠም ነገር ግን የቡድኑ ከፍተኛ ባለስልጣን ሀሰን ፋድላላህ ከሊባኖሱ አልጀዲድ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ “ቡድኑ ከጦርነቱ በኋላ ተጠናክሮ ይወጣል በሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያንም ትግሉን ይቀላቀላሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ አክለውም ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር የጀመረው ጦርነት ካበቃ በኋላ ንቁ ሆኖ እንደሚቀጥል፣ የተፈናቀሉ ሊባኖሶች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በመርዳት እና በእስራኤል ጥቃት የወደሙትን አካባቢዎች መልሶ መገንባት ላይ እንደሚያተኩር ተናግረዋል።
“ነገር ግን የእስራኤልን ተስፋፊነት በመቃወም የሚደረገው ትግል እንደማይቋረጥ ላረጋግጥ እወዳለሁ” ነው ያሉት።
ስምምነቱ ተሳክቶ ወደ ዘላቂ የተኩስ አቁም የሚገባ ከሆነ ከሊባኖስ ጦር የተሻለ የተዋጊዎች ቁጥር እና የውግያ አቅም እንዳለው የሚነገርለት ሄዝቦላህ በቀደመው ልክ ከእስራኤል ጋር ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ እንደማይገባ ይጠበቃል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሀማስ እና ከኢራን ጋር የሚኖረው ግንኙነት ምን ሊመስል እንደሚችል በጥያቄ ውስጥ እንደሚገኝ ሮይተርስ አስነብቧል።
እስራኤል በሊባኖስ ባወጀችው ጦርነት የቡድኑን መሪዎች ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮችን ገድላለች፡፡
ከዚህ ባለፈም ድንበር አቋርጣ በፈጸመችው የእግረኛ እና የአየር ጥቃት እስካሁን 3700 ንጹሀን ሲገደሉ 8.5 ቢሊየን የሚገመት ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አድርሳለች፡፡