“የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት አይቀሬ ነው ብዬ አላምንም” - የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር
ዋሽንግተን እስራኤል በሊባኖስ መዲና ቤሩት ላይ ጥቃት እንዳትፈጽም የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እየመራች ነው ተብሏል
እስራኤልና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ከ2006ቱ ጦርነት ወዲህ ከባድ የተኩስ ልውውጥ እያደረጉ ነው
የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ፍጥጫ በየእለቱ እየጨመረ ቢመጣም ወደለየለት ጦርነት ያመራል ብለው እንደማያምኑ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን ገለጹ።
ባለፈው ቅዳሜ በጎላን ኮረብታዎች ድሩዜ መንደር የተፈጸመውን ጥቃት የ12 ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈ በኋላ የሊባኖስና እስራኤል ውጥረት ተባብሷል።
እስራኤል በኢራን ሚሳኤል ጥቃቱን ፈጽሟል ያለችውን ሄዝቦላህ ይዞታዎች በጄቶች መደብደቧን ቀጥላለች።
ሄዝቦላህም በእስራኤል የተለያዩ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ በትናንትናው እለት ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።
የቤሩት አውሮፕላን ማረፊያ በውጥረቱ ምክንያት በረራዎችን እስከመሰረዝ መድረሱን ያወሳው ሬውተርስ የሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማይፈልግ መግለጫ ማውጣቱን ጠቁሟል።
ይሁን እንጂ እስራኤል የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የበርካታ ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው የቅዳሜው ጥቃት በኋላ የእግረኛ ጦሯን ወደ ሊባኖስ ማስገባት ትጀምራለች የሚለው ስጋት አይሏል።
አሜሪካም እስራኤል በሊባኖስ መዲና ቤሩት ጥቃት እንዳትፈጽምና ዋና ዋና የሲቪል መሰረተ ልማቶችን እንዳታፈራርስ ቴል አቪቭን ለማግባባት የሚደረገውን የዲፕሎማሲያዊ ጥረት እየመራች ነው ተብሏል።
የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን በፊሊፒንስ መዲና ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፥ “ምንም እንኳን በእስራኤልና ሊባኖስ ድንበር ያለው ውጥረት አሳሳቢ ቢሆንም ወደለየለት ጦርነት መግባታቸው አይቀሬ ነው ብዬ ግን አላምንም” ሲሉ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ዘመናዊ ጦር የታጠቁትን እስራኤልና ሄዝቦላህ ግጭት ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ ይቀጥላል ቢሉም ሀገራቸው እስካሁን ሁለቱን ተፋላሚዎች ለማሸማገል ስላደረገችው ሙከራ አላብራሩም።
እስራኤል ትናንት ምሽት በ10 የሄዝቦላህ ይዞታዎች ላይ በምሽት በፈጸመችው ጥቃት አንድ የቡድኑን ተዋጊ መግደሏን ያስታወቀች ሲሆን፥ ቡድኑም ግድያውን አረጋግጧል።
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለፍልስጤሙ ሃማስ አጋርነቷን ያሳየው ሄዝቦላህ በየቀኑ ወደ እስራኤል በሚተኩሳቸው ሚሳኤሎች ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
የእስራኤል ጦር በሄዝቦላህ ጥቃት እስካሁን 23 ንጹሃን እና 17 ወታደሮች ህይወታቸው ማለፉን ገልጿል።
በአንጻሩ እስራኤል በወሰደቻቸው የአጻፋ እርምጃዎች 350 የሚጠጉ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች እና ከ100 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን የሬውተርስ መረጃ ያሳያል።