ሄዝቦላ የወታራዊ አዛዡን ግድያ ለመበቀል በእስራኤል ላይ ሚሳይል አዘነበ
ጥቃቱን ተከትሎ የእስራኤል ካቢኔ ወደ ስብሰባ መግባቱን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቢሮ አስታውቋል
የሄዝቦላ ወታደራዊ አዛዥን እና የሀማስ ፖለቲካዊ መሪን ግድያ ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ውጥረት ተፈጥሯል
ሄዝቦላ የወታራዊ አዛዡን ግድያ ለመበቀል መጠነሰፊ የሚሳይል ጥቃት ማድረሱን አስታወቀ።
ሄዝባላ ባለፈው ወር በቤሩት በከፍተኛ ወታደራዊ አዛዡ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ለመበቀል በዛሬው እለት በእስራኤል ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች እና ድሮኖችን መተኮሱን በኢራን የሚደገፈው ቡድን አስታውቋል።
ሄዝቦላ ጥቃት መፈጸሙን ያስታወቀው የእስራኤል ካቢኔ ለጥቃቱ ምላሽ ለመስጠት ስብሰባ እያደረገ ባለበት ወቅት ነው።
የእስራኤል ጦር ሄዝቦላ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀ መሆኑን ስለደረሰበት፣ ሄዝቦላ ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት የእስራኤል ጄቶች ሊባኖስ ውስጥ አላማዎችን መትተዋል ብሏል ጦሩ።
ሄዝቦላ 320 ካትዩሻ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፉን እና 12 ወታደራዊ ኢላማዎችን መምታቱን ገልጿል። ለወታደራዊ አዛዥ ፉአድ ሽኩር ግድያ የሚሰጠውን የመጀመሪያውን ምዕራፍ ምላሽ ማጠናቀቁን የገለጸው ቡድኑ ሙሉ ምላሽ ለመስጠት ጊዜ ይፈጃል ብሏል።
ጥቃቱን ተከትሎ የእስራኤል ካቢኔ ወደ ስብሰባ መግባቱን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቢሮ አስታውቋል።የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ዮአቭ ጋላንት እስራኤል ራሷን ለመከላከል ሁሉንም ነገር ታደርጋለች ብለዋል።
"እስራኤላውያንን ከጥቃት ለመከላከል በሊባኖስ ውስጥ ኢላማውን የጠበቀ ጥቃት እያካሄድን ነው። በሊባኖስ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተልነው ነው፣ ዜጎቻችንን ለመከላከል በእጃችን ያለውን ሁሉ ለመጠቀም ወስነናል" ብለዋል ጋላንት ባወጡት መግለጫ።
አብዛኞቹ የእስራኤል ጥቃቶች በደቡባዊ ሊባኖስ ያሉ ኢላማዎች ላይ ያነጣጠሩ ቢሆኑም ጦሩ ስጋት ባለበት በየትኛውም ቦታ ጥቃት ለመሰንዘር ዝግጁ መሆኑን የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ጋላንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን በቴልአቪቭ ወደሚገኘው ቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ የሚገቡ እና የሚወጡ በረራዎች ተቋርጠዋል።
የሄዝቦላ ወታደራዊ አዛዥ ሹክር እና የሀማስ ፖለቲካዊ መሪ ሀኒየህን ግድያ ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ውጥረት ተፈጥሯል።