ብሪታንያ ለስደተኞች ቪዛ መከልከሏን ተከትሎ የሰራተኞች እጥረት እንዳጋጠማት ተገለጸ
በብሪታንያ በጤና እና እንክብካቤ ሙያ የሰራተኞች እጥረት አጋጥሟታል ተብሏል
የሰራተኛ እጥረቱ ያጋጠመው የቀድሞው የሀገሪቱ መንግስት ጥብቅ የስደተኞች ህግ በመከተሉ እንደሆነ ተገልጿል
ብሪታንያ ለስደተኞች ቪዛ መከልከሏን ተከትሎ የሰራተኞች እጥረት እንዳጋጠማት ተገለጸ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ሩሺ ሱናክ ይመራ የነበረው የቀድሞው የብሪታንያ መንግስት በስደተኞች ላይ ጥብቅ ህግ መከተሉ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎ በሀገሪቱ በተወሰኑ የስራ ዘርፎች ዙሪያ ከፍተኛ የሚባል የሰራተኞች እጥረት እንዳጋጠመ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ በተለይም በጤና እና እንክብካቤ ሙያ ዘርፎች የሰራተኞች እጥረቱ ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡
በትምህርት እና ሌሎች ምክንያቶች ከመላው ዓለም ወደ ብሪታንያ የሚገቡ ዜጎች ባለፉት ዓመታት ሆን ተብሎ እንዲቀንሱ የተደረጉ ሲሆን ይህም ለሰራተኞች እጥረት ካጋለጡ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው ተብሏል፡፡
ብሪታንያ በተያዘው የ2024 ዓመት ውስጥ እስከ ሰኔ ወር ድረስ ለ89 ሺህ ዜጎች የጤና እና እንክብካቤ ሙያ ዘርፍ ቪዛ ሰጥታለች፡፡
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በ81 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል፡፡
አዲሱ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ኬር ስታርመር ማን ናቸው?
በብሪታንያ በማህበራዊ ዘርፎች ከፍተኛ የሰራተኞች እጥረት እንዳያጋጥም የሀገሪቱ መንግስት ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የብሪታንያ ዩንቨርሲቲዎች በየዓመቱ ከመላው ዓለም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን የሚቀበሉ ሲሆን ቪዛ ያገኙ ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸውን ወደ ብሪታንያ እንዲያስመጡ ፈቀድላቸው ነበር፡፡
ይህን እድል የቀድሞው የብሪታንያ አስተዳድር መከልከሉ በሀገሪቱ ላጋጠመው የሰራተኛ እጥረትም ሌላኛው ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል፡፡