የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከብሔራዊ ደህንነት አማካሪዎቻቸው ጋር በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ዙርያ መክረዋል
የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላ ዛሬ ጠዋት በእስራኤል የሮኬት እና የድሮን ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ፡፡
በሰሜናዊ እስራኤል በሁለት ወታደራዊ ስፍራዎች ላይ እና በእስራኤል ወታደራዊ ተሸከርካሪ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነው ሄዝቦላ ያስታወቀው፡፡
የእስራኤል መከላከያ ጦር በደረሰው ጥቃት ናህሪያ በተባለችው የወደብ ከተማ ላይ በንጹሀን ዜጎች ላይ መጠኑ በውል ያልታወቀ ጉዳት መድረሱን አረጋግጧል፡፡
የመከላከያ ሀይሉ ከሊባኖስ የተነሱ ድሮኖች የሀገሪቱን የአየር ክልል በማለፍ በከተማዋ ዋና መንገዶች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ያስታወቀ ሲሆን አንድ ድሮን በእስራኤል የአየር መቃወሚያ ተመታ መውደቋን ገልጿል፡፡
በተጨማሪም የአየር ሀይሉ በደቡባዊ ሊባኖስ በሁለት የሂዝቦላ ተቋማት ላይ በወሰደው የአጸፋ ምላሽ አራት የሂዝቦላ ታጣቂዎችን መግደሉን አስታውቋል፡፡
ሂዝቦላ በበኩሉ ባሳለፍነው ሳምንት እስራኤል ለገደለችው ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ የሚወስደውን የበቀል እርምጃ ገና እንዳልተጀመረ እና በቀጣይ ተከታታይ የተጠናከረ ጥቃት በእስራኤል ላይ እንደሚፈጽም ዝቷል፡፡
የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ መሪ እስማኤል ሀኒየህ እና የሂዝቦላ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ፉአድ ሹክር መገደላቸውን ተከትሎ ቴህራን እና ሄዝቦላ በቴልአቪቭ ላይ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በውጥረት ላይ የሚገኝው የመካከለኛው ምስራቅ ወደለየለት ቀጠናዊ ጦርነት እንዳያመራ ከፍተኛ ስጋት አንዣቦበታል፡፡
አሜሪካ፣ ብሪታንያና ካናዳ እና ሌሎችም ሀገራት ዜጎቻቸው ከሊባኖስ ለቀው እንዲወጡ በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም አየር መንገዶች ወደ ቀጠናው የሚያደርጉትን በረራ በመሰረዝ ላይ ናቸው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከብሔራዊ ደህንነት አማካሪዎቻቸው ጋር መክረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሄዝቦላ በእስራኤል ላይ ጥቃት የሚሰነዘር ከሆነ በምን አይነት መልኩ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚችል ከአማካሪዎቻቸው ገልጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
በተጨማሪም ኢራን ትፈጽመዋለች ተብሎ የሚጠበቀው የአጸፋ ምላሽ ምን አይነት ሊሆን እንደሚችል በግልጽ ባይታወቅም ለሁሉም አይነት ጥቃቶች ምላሽ መስጠት በሚያስችል ቁመና ለእስራኤል ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ነው ፕሬዝዳንቱ ያስታወቁት፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው ግጭቱ ወደ ቀጠናዊ ጦርነት ከማምራቱ በፊት የዲፕሎማሲ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የውጥረቶች መባባስ ወደለየለት ግጭት ከማስገባት ያለፈ ጥቅም የለውም ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ሁሉም አካላት ወደ ግጭት ከሚያስገቡ ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጠይቀዋል፡፡
በቅርቡ እስራኤል በሶርያ በሚገኝ የኢራን ኢምባሲ ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ቴህራን በወሰደችው የአጸፋ ምላሽ 300 ድሮን እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል፡፡