ሄዝቦላ በእስራኤል ላይ የሮኬት እና ከባድ መሳሪያ ጥቃት ማድረሱን በድጋሚ ጀመረ
ሄዝቦላ እና እስራኤልም 10 ወራትን ካስቆጠረው የጋዛ ጦርነት ጎን ለጎን ተኩስ ሲለዋወጡ ቆይተዋል
በሰሜን እስራኤል በሚገኙ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ሁለት ሄዝቦላ የከባድ መሳሪያ እና ሁለት የሮኬት ጥቃቶችን አድርሻለሁ ብሏል
ሄዝቦላ በእስራኤል ላይ የሮኬት እና ከባድ መሳሪያ ጥቃት ማድረሱን በድጋሚ ጀመረ።
በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው የሄዝቦላ ኃይሎች በትናንትናው እለት በእስራኤል ላይ የሮኬት እና የከባድ መሳሪያ ጥቃት ማድረስ በመጀመራቸው፣ እስራኤል የቡድኑን አዛዥ በቤሩት ከገደለች በኋላ በድንበር አካባቢ ጋብ ብሎ የነበረው ሁኔታ አብቅቷል።
ሄዝቦላ በሊባኖስ የአየር ክልል ሲበር በነበረ የእስራኤል የጦር አውሮፕላን ላይ ከመሬት የሚተኮስ ሚሳይል ማስወንጨፉን እና እንዲመለስ ማስገደዱን ገልጿል።
ከዚህ በተጨመሪም በሰሜን እስራኤል በሚገኙ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ሁለት የከባድ መሳሪያ እና ሁለት የሮኬት ጥቃቶችን አድርሻለሁ ብሏል ሄዝቦላ።
የእስራኤል ጦር ባወጣው መግለጫ ከሊባኖስ የመጣን የአየር ኢላማን በእስራኤል ይዞታ ስር በሚገኘው ጎላን ሀይት ውስጥ በተሳካ ሁኔታ ማክሸፉን አስታውቋል።
ሮይተርስ የሊባኖስ ሚዲያዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ እስራኤል በትናንትናው እለት በፈጸመች የአየር እና የከባድ መሳሪያ ጥቃት በደቡብ ሊባኖስ የሚገኙ በርካታ መንደሮች ተደብድበዋል።
የእስራኤል ጦር በደቡብ ሊባኖስ ሁለት የሄዝቦላ ተዋጊዎችን መትቻለሁ ብሏል። የሄዝቦላ መሪ ሰኢድ ሀሰን ነስረላህ ባለፈው ማክሰኞ እለት ፉአድ ሹክር የተባለ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ በእስራኤል የአየር ጦቃት መገደሉን ተከትሎ ለተጎጂዎች ክብር ሲባል እና ቀጣይ ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ለማሰብ በድንበር ግጭት እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።
በቤሩት ደቡባዊ ጫፍ በሚገኘው የሄዝቦላ ዳሂየህ ምሽግ ላይ በደረሰ ጥቃት የኢራን ወታደራዊ አማካሪ እና አምስት ንጹሀን ተገድለዋል። ነስራላህ ግድያን እንደሚበቀሉ እና ምን አይነት ይሁን የሚለው ግን እየተጠና መሆኑን ተናግረዋል።
ሄዝቦላ እና እስራኤልም 10 ወራትን ካስቆጠረው የጋዛ ጦርነት ጎን ለጎን ተኩስ ሲለዋወጡ ቆይተዋል። እስራኤል እና አሜሪካ በጎላን ሀይት ለደረሰው እና የ12 ታዳጊዎችን ህይወት ለቀጠፈው ጥቃት ሄዝቦላን ተጠያቂ ያደርጋሉ፤ ሄዝቦላ ግን እጅ እንደሌለበት አስተባብሏል።