እስራኤል በሊባኖስ ላይ ጦርነት ብታውጅ የሚደርስባትን ታውቀዋለች - ናስራላህ
አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችና ድሮኖችን የታጠቀው ሄዝቦላህ ለእስራኤል ማስፈራሪያ ቦታ እንደማይሰጠውም ነው የሄዝቦላህ መሪ የተናገሩት
እስራኤል ወደ ሊባኖስ እግረኛ ጦሯን በማስገባት ሄዝቦላህን ለመደምሰስ መዘገጀቷን መግለጿ ይታወሳል
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ ወደ ሊባኖስ እግረኛ ጦሬን አስገባለሁ ያለችውን እስራኤል አስጠንቅቀዋል።
እስራኤል በሊባኖስ ላይ ጦርነት ካወጀች “እኛም ወደ ደቡባዊ እስራኤል የማንገባበት ምንም ህግም ሆነ ገደብ የለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ሄዝቦላህ በድሮን የቀረጸውን በደቡባዊ እስራኤል ሃይፋ የሚገኙ ወታደራዊ ስፍራዎች የሚያሳይ ቪዲዮ መልቀቁን ተከትሎ እስራኤል ወደ ሊባኖስ እግረኛ ጦሯን ለማስገባት መዘጋጀቷን አስታውቃለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፥ “ሄዝቦላህን የሚደመስስና ሊባኖስንም ክፉኛ የሚጎዳ የለየለት ጦርነት ውስጥ ለመግባት ተቃርበናል” ማለታቸውን ሲኤንኤን በዘገባው አስታውሷል።
የሄዝቦላህ መሪው ናስራላህ ግን “በእስራኤል ሚዲያዎች እየተላለፉ የሚገኙ በሊባኖስ ጦርነት እንከፍታለን ማስፈራሪያዎች አይረብሹንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገርለት ቡድኑ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን መታጠቁንና በራሱ አቅም በርካታ ድሮኖችን መስራቱንም ነው የጠቀሱት።
“ጠላቶቻችን (እስራኤል) ለከባድ ጊዜ በሚመጥን ደረጃ ያደረግነውን ዝግጅት ያውቁታል፤ የድሮን እና ሮኬት ጥቃታችን ሊቋቋሙት አይችሉም፤ ዝግጅታችን ስለሚረዱም ነው እስካሁን ጦራቸውን ያላስገቡት” ሲሉም አብራርተዋል።
በሊባኖስ ድንበር እየተካሄደ ያለው ጦርነት እስራኤል ሙሉ ትኩረትና ሃይሏን ጋዛ ላይ እንዳታደርግ በማድረግ ልዩነት መፍጠሩን የገለጹት ናስራላህ፥ እስራኤል በጋዛ ድብደባዋን እስካላቆመች ድረስ ሄዝቦላህ ጥቃቱን ይቀጥላል ብለዋል።
ናስራላህ በቴሌቪዥን በተላለፈ መልዕክታቸው ለእስራኤል አጋር ሆናለች ያሏትን ቆጵሮስም አስጠንቅቀዋል።
የእስራኤል ጦር የደቡባዊ ሊባኖስ አይነት መልካምድር ባለው የቆጵሮስ መሬት ላይ ወታደራዊ ልምምድ እያደረገ መሆኑን ደርሰንበታል ያለው የሄዝቦላህ መሪ፥
ቆጽሮስ ለእስራኤል ጄቶች አውሮፕላን ማረፊያዎቿን ክፍት ካደረገች “በእስራኤል ላይ የምናውጀው ጦርነት አካል ትሆናለች” ሲሉ አሳስበዋል።
ከሊባኖስ በ200 ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ የምትገኘው የቆጽሮስ ደሴት የአውሮፓ ህብረት አባል ስትሆን፥ ከ2014 ጀምሮ ከእስራኤል ጋር ወታደራዊ ልምምድ እያደረገች ነው።
የቆጵሮስ ፕሬዝዳንት ኒኮስ ክሪስቶዱልዲስ በሄዝቦላህ የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርገውታል።
ቆጵሮስ በባህር ወደ ጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ ለማስገባት እንደ መተላለፊያ ኮሪደር በመሆን ማገልገሏን እንደምትቀጥል በመጥቀስም “የጦርነቱ አካል አይደለንም” ብለዋል።