ሩሲያ እስራኤል በሶሪያ የምትፈጽመውን የአየር ላይ ጥቃቷን እንድታቆም ማስጠንቀቋ ተሰማ
የሞስኮ ማስጠንቀቂያ የተሰማው እስራኤል በሶሪያ የሩሲያ ጦር ማዘዣ በሚገኝበት ላታኪያ ወደብን መደብደቧን ተከትሎ ነው
እስራኤል ከሩሲያ ማስጠንቀቂያ በኋላ በወደቧ ላይ ድብደባዋን ቀንሳለች ተብሏል
ሩሲያ እስራኤል በሶሪያ የምትፈጽመውን የአየር ላይ ጥቃቷን እንድታቆም ማስጠንቀቋ ተሰማ።
ከ13 ወራት በፊት ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።
የሊባኖሱ ሂዝቦላህ ከሐማስ ጎን መቆሙን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ከጋዛ በተጨማሪ ወደ ሊባኖስ ገብቶ ጦርነት መክፈቱም ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ሂዝቦላህ በሶሪያ በኩል የጦር መሳሪያ ድጋፍ ያገኝበታል ተብሎ በሚታሰበው ላታኪያ ወደብ ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።
የሶሪያዋ የላታኪያ ወደብ ከተማ የፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ደጋፊ ስትሆን የሩሲያ ጦር ማዘዣም ነች።
በዚህ ምክንያትም ሩሲያ እስራኤል በላታኪያ የወደብ ከተማ የአየር ላይ ድብደባዋን እንድታቆም መጠየቋ ተገልጿል።
የፕሬዝዳንት ፑቲን መካከለኛው ምስራቅ ልዩ አማካሪ አሌክሳንደር ላቭሬንቲቭ ለሪያ ኖቮስቲ እንዳሉት "እስራኤል የሩሲያ ጦር ማዘዣ አቅራቢያ ጥቃት ሰንዝራለች፣ በስፍራው ያለው ጦራችን ለእስራኤል ባለስልጣናት በስፍራው እያደረሰች ያለው ጥቃት ተቀባይነት የለውም ብሎ አሳውቋል" ብለዋል።
"የእስራኤል ጦር በጥቅምት ወር ላይ ያደረሰውን ጥቃት አሁን ይደግመዋል ብለን አንጠብቅም ሲሉም አማካሪው ተናግረዋል።
በላታኪያ ወደብ አቅራቢያ ያለው የሩሲያ ጦር ለሂዝቦላህ የጦር መሳሪያ እያቀረበ እንዳልሆነም ተገልጿል።
ሶሪያ ከኢራን ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላት ሲሆን ሂዝቦላህ በደማስቆ በኩል የጦር መሳሪያ እየደረሰው ነው በሚል እስራኤል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አድርሳለች።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድር በአካባቢው የተኩስ አቁም እንዲደረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለዶናልድ ትራምፕ ስጦታ መስጠት እንደምትፈልግ እየተዘገበ ይገኛል።