ቴህራን በቅርቡ "ራዝቫን" የተሰኘ አጥፍቶ ጠፊ ድሮን ማስተዋወቋ ይታወሳል
የኢራን ጦር 1 ሺህ አዳዲስ ድሮኖችን መረከቡ ተነገረ።
ታስኒም የዜና ወኪልን ጠቅሶ ሬውተርስ እንደዘገበው የኢራን ጦር አዳዲሶቹን ድሮኖች ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ማሰራጨት ጀምሯል።
በኢራን ጦር እና ተመራማሪዎች በሀገሪቱ የተመረቱት ድሮኖች ከቀደምቶቹ የተሻለ አቅም እንዳላቸው የጠቀሰው ታስኒም ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም።
"እስከ 2 ሺህ ኪሎሜትሮች መጓዝ የሚችሉት ድሮኖች ከፍተኛ የማውደም ሃይል አላቸው፤ የአየር መቃወሚያዎችን የማለፍ አቅማቸውም ከፍተኛ ነው" ብሏል የዜና ወኪሉ።
አዳዲሶቹ ድሮኖች የኢራን ጦር የሚያካሂዳቸውን ዘመቻዎች በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖራቸውም ተመላክቷል።
ኢራን በኒዩክሌር ፕሮግራሟ ምክንያት በምዕራባውያን በሺዎች የሚቆጠሩ ማዕቀቦች ቢጣሉባትም በርካታ ሚሳኤሎችና ድሮኖችን በማምረት ላይ ትገኛለች።
ቴህራን ባለፈው ሳምንትም "ራዝቫን" የተሰኘ አጥፍቶ ጠፊ ድሮንም ማስተዋወቋ ይታወሳል።
"ራዝቫን" ከእስራኤሉ "ዩቪሽን" ድሮን ጋር ተመሳሳይ ቅርጽ አለው የሚሉ ባለሙያዎች ኢራን አዳዲስ የፈጠራ ውጤት እያለች የምታቀርባቸው ድሮኖች ከሌሎች ሀገራት የተቀዱ መሆናቸው ይናገራሉ።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ በድሮን ቴክኖሎጂ የተመዘገበው ስኬት ሀገሪቱ ማዕቀቦችን አልፋ ፍላጎቷን ማሳካት እንደምትችል ያሳየችበት ነው ይላል።
ኢራን ከባላንጣዋ እስራኤል ሊቃጣባት ለሚችል ጥቃት ራሷን ስታዘጋጅ ለድሮን ትልቅ ስፍራ መስጠቷን ደጋግማ ገልጻለች።
በመስከረም ወር 2024 ይፋ ያደረገችው "ሻሄድ-136 ቢ" የተሰኘ ድሮን ማስተዋወቋ የሚታወስ ነው።
"ሻሄድ-136 ቢ" እስከ 4 ሺህ ኪሎሜትሮች በመጓዝ ጥቃት ማድረስ የሚችል ነው የተባለ ሲሆን፥ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያንም "አሁን የመከላከል አቅማችን አድጓል፤ ማንም ኢራንን መውረር አያስብም" ሲሉ መናገራቸውም አይዘነጋም።
ኢራን በጥር ወር መጀመሪያ ለሁለት ወራት የሚቆይ ወታደራዊ ልምምድ ጀምራለች።
የናታንዝ የኒዩክሌር ጣቢያን ጨምሮ ዋና ዋና መሰረተ ልማቶች ላይ ሊደርስ የሚችል ጥቃትን መከላከል የሚያስችሉ ልምምዶችም መካሄዳቸውን ቀጥለዋል።