በሳኡዲ ሊግ ከፍተኛ ክፍያ የሚከፈላቸው አፍሪካውያን ተጫዋቾች
ሞሀመድ ሳላህ እና ሳዲዮ ማኒ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ክፍያ ከሚከፈላቸው አፍሪካውያን ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳሉ
በሳኡዲ ሊግ በመጫወት ላይ የሚገኙ አፍሪካውያን እስከ 1 ሚሊየን ዶላር ሳምንታዊ ደመወዝ ያገኛሉ
አፍሪካ ለአለም አቀፍ እግር ኳስ ትርዒት ልዩ ችሎታ ያላቸውን ባለተሰጥኦ ተጫዋቾች በማበርከት ከሚታወቁ የአለም ክፍሎች መካከል አንዷ ናት፡፡
በስፔን፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝ እና ሌሎችም ተወዳጅ የአውሮፓ ሊጎች ባለፉት አስርት አመታት አፍሪካውን እግር ኳስ ተጫዋቾች ደምቀው ታይተዋል፡፡
በተለያዩ የውድድር መድረኮች በብቃታቸው ተፈላጊነታቸው እየጨመረ የመጣው አፍሪካውያን የሚያገኙት ገቢም በዛው ልክ እያደገ ይገኛል፡፡
የፎርብስ መጽሔት ከፍተኛ ክፍያ ከሚያገኙ 10 እግር ኳስ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ግብጻዊውን ሞሀመድ ሳላህ እና ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኒን አካቷል፡፡
በቅርቡ ከአውሮፓ እግር ኳስ ጋር መፎካከር የሚችል ተወዳጅ ሊግን ለመገንባት ጥረት እያደረገች የምትገኘው ሳኡዲ አረብያ የበርካታ የአፍሪካውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች ማረፊያ እየሆነች ነው፡፡
በሊጉ ውስጥ ከፍተኛ ክፍያ ከሚያገኙ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል ለአል አህሊ የሚጫወተው አልጄሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ ቀዳሚው ነው፡፡
አልጄሪያዊው የቀድሞ የማንችስተር ሲቲ ተጫዋች በሳኡዲው ክለብ 858 ሺህ 944 ፓውንድ ሳምንታዊ ደመወዝ የሚከፈለው ሲሆን ወደ ዶላር ሲቀየር ከአንድ ሚሊየን ዶላር ይሻገራል፡፡
የቀድሞው የሊቨርፑል አጥቂ በአሁኑ ወቅት ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር በአል-ናስር የተጣመረው ሳዲዮ ማኔ በ658 ሺ ፓውንድ ሳምንታዊ ደመወዝ ሁለተኛው ከፍተኛ ተከፋይ ነው፡፡
ካሊዱ ኩሊባሊ፣ ሴኮ ፎፋና እና ፍራንክ ኬሲ በቅደም ተከተል ከሶስት እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡