በ2025 መጀመሪያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር መገኛ የሆኑ የአለም ሀገራት
በ2024 የአለም የህዝብ ቁጥር በ71 ሚሊየን ያደገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ቁጥሩ 8.05 ቢሊየን ደርሷል
በህዝብ ብዛት ህንድ ቀዳሚውን ደረጃ ስትይዝ ኢትዮጵያ 10ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች
የአለም የህዝብ ቁጥር በየሰከንዱ 4.2 በመቶ ውልደትን እያስመዘገበ በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ እያሳየ ቀጥሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ፣ ናይጄሪያ ፣ ግብጽ ፣ አሜሪካ እና ባንግላዲሽን ጨምሮ 12 ሀገራት ከ100 ሚሊየን በላይ ህዝብ የሚገኝባቸው ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2050 ሩሲያ እና ጃፓን የህዝብ ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ሲሄድ የተቀሩት ሀገራት ቢያንስ እስከ 2050 እድገታቸውን እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል ።
በተጨማሪም ከ 99 ሚሊየን በላይ ህዝብ የሚገኝባቸው ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ቬትናም በቅርቡ100 ሚሊየንን እንደሚሻገሩ ይጠበቃል፡፡
ምንም እንኳን መሰል ሀገራት በህዝብ ቁጥር 100 ሚሊየንን እየተሻገሩ ቢሆንም 800 የማይሞሉ ዜጎች የሚገኙባት ቫቲካን ሲቲን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ከ100 ሚሊየን ያነሰ ህዝብ ነው ያላቸው፡፡
ወርልድ ፖፕሌሽንሪቪው ባወጣው መረጃ በ2025 መጀመሪያ አንድ ቢሊየንን የተሻገሩ ሁለት ሀገራት ፣ ከ100 - 999 ሚሊየን 12 ሀገራት ፣ ከ10-99.9 ሚሊየን 80 ሀገራት ፣ ከ1-9.9 ሚሊየን 66 ሀገራት ፣ ከአንድ ሚሊየን በታች የህዝብ ቁጥር ያላቸው ደግሞ 74 ሀገራት እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡
እድገቱ በተከታታይ አመት 140 ሚሊየን አዳዲስ ህጻናትን እያስመዘገበ የቀጠለ ሲሆን በ2050 አጠቃላይ የህዝብ 9.7 ቢሊየንን እንደሚሻገር ይጠበቃል፡፡
በዚሁ አመት ከአለም አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር ግማሽ ያህሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በስምንት ሀገራት የሚገኝ ይሆናል፡፡
በአለም የህዝብ ቁጥር ብዛት የቀዳሚነት ደረጃውን ከቻይና የተረከበችው ህንድ በ2025 በ1.450 ቢሊየን የህዝብ ቁጥር መሪነቷን ይዛ ቀጥላለች፡፡
1.419 ቢሊየን ህዝብ ባለቤት የሆነችው ቻይና በሁለተኛነት የምትከተል ሲሆን አሜሪካ ፣ ኢንዶኔዥያ እና ፓኪስታን በ100 ሚሊየኖች በተከታታይ ደረጃውን ይዘዋል፡፡
ከአፍሪካ ናይጄሪያ እና ኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ካላቸው 10 የአለም ሀገራት ውስጥ አፍሪካን ወክለው ተካተዋል፡፡
በደረጃው 232 ሚሊየን ህዝብ ያላት ናይጄሪያ 6ተኛ ስትሆን የ132 ሚሊየን ህዝብ መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በ10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡