10 ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ሀገራት
ታዋቂው የሳይበር ደህንነት ተቋም ሲዮን ኢትዮጵያ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭነታቸው ከፍ ካሉ ሀገራት አካቷታል
ኢትዮጵያ ባለፈው አመት 7 ሺህ የሚጠጉ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተደርገውባታል
አለማችን በኢንተርኔት መተሳሰሯ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ጥገኝነቷ በፍጥነት እያደገ መሄዱን ተከትሎ የሳይበር ጥቃትም ፈተና ሆኖባታል።
ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ከ340 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ተጎጂ ያደረጉ የሳይበር ጥቃቶች መፈጸማቸውን የፎርብስ መረጃ ያሳያል።
ከ2021 እስከ 2023 የተመዘገበው የመረጃ ምንተፋ ካለፉት አመት በ72 በመቶ ማደጉም ቴክኖሎጂው ይዞት የመጣው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል።
ግለሰቦችን፣ ተቋማትን እና የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ኢላማ ባደረጉ የሳይበር ጥቃቶች በ2023 ብቻ ከ8 ትሪሊየን ዶላር በላይ የሚገመት ጉዳት ደርሷል።
የሳይበር ጥቃት የትኛውንም ሀገር ወይም ተቋም ለይቶ እንደማይተው የሚገልጸው ታዋቂው የሳይበር ደህንነት ተቋም ሲዮን፥ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ህግና ቴክኖሎጂ ያላቸው ሀገራት አደጋውን መቀነስ ችለዋል ይላል።
በአንጻሩ ደካማ የሳይበር ደህንነት ህግ ያላቸው አልያም ከነጭራሹ የሌላቸውና ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመመከት የሚጠቀሟቸው ቴክኖሎጂዎች ከፈጣኑ የዲጂታል አለም ጋር አብሮ በማይሄድባቸው ሀገራት አደጋው ሲከፋ ይታያል።
ተቋሙ የተለያዩ መመዘኛዎችን በመጠቀም የሀገራትን የሳይበር ደህንነት ደረጃ ይፋ ያደርጋል።
በዚህም መሰረት ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው በሚል ከተጠቀሱ ሀገራት ኢትዮጵያ በ8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም 6 ሺ 959 የሳይበር ጥቶች መፈጸማቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) መግለጹ ይታወሳል።
ከሳይበር ጥቃቶቹ ውስጥ 2 ሺ 559 ያህሉ በድረ ገጽ፤ 1 ሺህ 493ኙ ደግሞ መሰረት ልማት የማቋረጥ (አብዛኛው የፋይናንስ ተቋማትን ኢላማ ያደረገ) እንደነበር አሳውቆ ነበር።
የሳይበር ጥቃት ሙከራዎቹን በመከላከል 23.2 ቢሊየን ብር ኪሳራ ማዳን ተችሏል መባሉም አይዘነጋም።
በሲዮን ጥናት መሰረት ቤልጂየም፣ ፊንላንድ እና ስፔን ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭነታቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ሀገራት ከፊት ተቀምጠዋል።