በአፍሪካ ብሄራዊ ምክርቤቶች (ፓርላማ) የሴቶች ድርሻ
ሴቶች ከአለማችን ህዝብ ግማሹን ቢይዙም በህግ አውጪ ምክርቤቶች ያላቸው ውክልና 27 በመቶ ብቻ ነው

ከ60 በመቶ በላይ የምክርቤት አባላቷ ሴቶች የሆኑባት ሩዋንዳ በአፍሪካ ብሎም በአለም ቀዳሚ ናት
የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በኋላ እድገት እያሳየ መጥቷል።
እንደ ኒውዝላንድ፣ ፊንላንድ እና አሜሪካ ያሉ ሀገራት የሴቶችን የመምረጥና ተመርጠው ስልጣን የመያዝ መብት በማረጋገጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ሴቶች ከአለማችን ህዝብ ግማሹን ቢይዙም በአለማቀፍ ደረጃ በህግ አውጪ ምክርቤቶች ያላቸው ውክልና በአማካይ 27 በመቶ ብቻ ነው። አሃዙ ከ20 አመት በፊት ከነበረበት የ12 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም አሁንም ገና ብዙ የሚቀረው እንዳለ ያሳያል።
በአፍሪካ በብሄራዊ የህግ አውጪ ምክርቤቶች (ፓርላማ) የሴቶች ውክልና በ2024 26 በመቶ መድረሱን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ከ60 በመቶ በላይ የምክርቤት አባላቷ ሴቶች የሆኑባት ሩዋንዳ በአፍሪካ ብሎም በአለም ቀዳሚውን ደረጃ ይዛ ቀጥላለች።
ደቡብ አፍሪካ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ኢትዮጵያ፣ ሴኔጋልና ናሚቢያ ከ40 በመቶ በላይ የምክርቤት አባላቸውን ሴቶች በማድረግ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በካቢኔያቸው ውስጥ ሴቶችን ማካተታቸውን የሚያነሳው የቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ በወንዶች የበላይነት የተያዘውን የፖለቲካ ዘርፍ አካታች ለማድረግ ኋላቀር አስተሳሰብን መዋጋት እንደሚገባ ያትታል።
የአለም የሴቶች ቀን "ማርች 8" ዛሬ ተከብሮ ሲውልም የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ተመክሯል።