ልጅ ላለመውለድ ሲሉ ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ ኬንያዊያን ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ነው ተባለ
ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ16 ሺህ በላይ ኬንያዊያን ሴቶች በራሳቸው ፈቃድ ልጅ ላለመውለድ ሲሉ የማይቀለበስ ቀዶ ጥገና ህክምና አድርገዋል

ቀዶ ህክምናው በወጣት ሴቶች መዘውተሩ ደግሞ ጉዳዩ ዋነኛ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል
ልጅ ላለመውለድ ሲሉ ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ ኬንያዊያን ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ነው ተባለ፡፡
በጎረቤት ሀገር ኬንያ ልጅ መውለድ የማይፈልጉ ሴቶች እርግዝና እንዳይፈጠር የሚያደርግ የቀዶ ህክምና እያደረጉ ናቸው ተብሏል፡፡
በኬንያ ልጅ መውለድ የማይፈልጉ ሴቶች በራሳቸው ፈቃድ ማህጸናቸውን የሚያስቋጥሩ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ይህ የማህጸን ማስቋጠር የወሊድ መከላከያ ዘዴ ሲሆን ከዚህ በፊት ልጅ የወለዱ እና ተጨማሪ ልጆችን መውለድ በማይፈልጉ ሴቶች የሚዘወተር ነበር፡፡
ይህ የወሊድ መቆጣጠሪያ ህክምና በተለምዶ ማህጸን ማስቋጠር በመባል የሚታወቅ ሲሆን አንዴ ህክምናው ከተሰጠ ዳግም መመለስ የማይቻል ነው፡፡
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንድም ልጅ ያልወለዱ ሴቶች ይህን የወሊድ መከላከያ ዘዴ የሚጠቀሙ ኬንያዊያን ወጣት ሴቶች ዘንድ እየተለመደ መጥቷል ተብሏል፡፡
የኬንያ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ከሆነ ባለፉት ሶስት ዓመታ ውስጥ ከ16 ሺህ በላይ ኬንያዊን ሴቶች ለዘለቄታው ልጅ መውለድ የማያስችላቸውን ይህን ማህጸን የማስቋጠር ህክምና ወስደዋል፡፡
ህክምናውን ካደረጉ ኬንያዊያን መካከል አንዷ የሆነችው የ28 ዓመቷ ኔሊ ሲሮንካ እንዳለችው ማህጸኔን ካስቋጠርኩ በኋላ እና ልጅ እንደማልወልድ ካወቅሁ በኋላ ነጻ የወጣሁ ያህል ተሰምቶኛል ብላለች፡፡
በናይሮቢ ባለ አንድ የግል ሆስፒታል ውስጥ የጽንስ እና ማህጸን ሐኪም የሆነው ዶክተር ቦሲሬ ለቢቢሲ እንዳለው ማህጸን የማስቋጠር የወሊድ መከላከያ ህክምና ከዚህ በፊት ልጆቻቸውን መጥነው እና ወልደው የጨረሱ እናቶች ቢሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጥቂት ልጆችን የወለዱ እና ምንም ልጅ የሌላቸው ሴቶችም እየወሰዱት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህን የወሊድ መከላከያ ህክምናን ለማግኘት በኬንያ ለአንድ ሴት በአማካኝ 230 ዶላር ክፍያን ይጠይቃል፡፡