በእስያ ያሉ 12 ወንዞች ከ1 ቢሊዮን በላይ ህዝብን አደጋ ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ ተገለጸ
በሂማሊያ እና አካባቢው ያለው ግግር በረዶ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየቀለጠ ነውም ተብሏል
በ100 ዓመታት ውስጥ ምድር ያላትን ግግር በረዶ የማጣት አደጋ ተጋርጦባታል
በእስያ ያሉ 12 ወንዞች ከ1 ቢሊዮን በላይ ህዝብን አደጋ ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ ተገለጸ፡፡
በህንድ የሚገኘው ሂማሊያ ተራራ በብዝሃ ህይወት አበርክቶው ጠቃሚ እንደሆነ የሚገለጽ ሲሆን ለበርካታ የዓለማችን ወንዞችም መነሻ በመሆን ያገለግላል፡፡
ከሂማሊያ ተራራ ተነስተው በርካታ ሀገራትን የሚያቋርጡ ወንዞች ያሉ ሲሆን በህ ተራራ ላይ ያለው ግግር በረዶ የዓለምን የአየር ንብረት ሚዛን ከሚያስጠብቁ ሀብቶች መካከልም አንዱ ነው፡፡
ተመራማሪዎች እንዳሉት ከሆነ በዚህ ተራራ ላይ ያለው ግግር በረዶ በፍጥነት እየቀለጠ ሲሆን ይህም በእስያ ያሉ ከ12 በላይ ወንዞችን በዉሃ እንዲሞሉ በማድረግ ከ1 ቢሊዮን በላይ ዜጎችን ህይወት አደጋ ውስጥ እንደሚጥል ተገልጿል፡፡
በሂማሊያ ተራራ ላይ ያለው ግግር በረዶ አሁን ባለበት የመቅለጥ ፍጥነት ከሄደ የያዝነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት 75 በመቶ በረዶው ይቀልጣል ተብሏል፡፡
በሂማሊያ ተራራ ላይ ያለው በረዶ መቅለጥ በቀጥታ በአካባቢው ባሉ 250 ሚሊዮን ዜጎችን ለውሃ እጥረት እና ጎርፍ እንደሚያጋልጥ ተመራማሪዎቹ ጠቅሰዋል፡፡
የከርሰ ምድር ተመራማሪው ፊሊፕ ዌስተር እንዳሉት አሁን ባለንበት ሁኔታ ከቀጠልን በ100 ዓመት ውስጥ በምድር ላይ ያሉንን ግግር በረዶ እናጣለን ብለዋል፡፡
በተለይም አፍጋኒስታን፣ ባንግላዲሽ፣ ቡታን፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ምያንማር፣ ኔፓል እና ፓኪስታን ደግሞ በሂማሊያ ተራራ እና አካባቢው ባለው የበረዶ መቅለጥ ምክንያት በውሀ ይጥለቀለቃሉ ተብሎ ስጋት ውስጥ ያሉ ሀገራት ናቸው፡፡
አሁን ላይ ይህ አካባቢ ሙቀቱ እየጨመረ መጥቷል የተባለ ሲሆን የምድር ሙቀት ሶስት ዲግሪ ሴልሺየስ ሲደርስ አካባቢው 80 በመቶ ግግር በረዶውን ከማጣቱ በተጨማሪ በጎርፍ ክፉኛ ይጥለቀለቃል ተብሏል፡፡