የተሳከለት የምርጫ ውጤት ገማቹ ተመራማሪ ስለ2024ቱ የአሜሪካ ምርጫ ምን አለ?
የታሪክ ተመራማሪው አለን ሊችማን ካለፉት 10 የአሜሪካ ምርጫዎች በዘጠኙ ግምቱ ሰምሮ ያሸንፋል ያለው እጩ ዋይትሃውስ መዝለቁ ተነግሯል
ሊችማን ለግምቱ “13 ቁልፍ” መመዘኛ መስፈርቶችን እንደሚጠቀም አስታውቋል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊን በመገመት የተሳካለት የታሪክ ተመራማሪ አለን ሊችማን በህዳሩ ወር ምርጫ ምክትል ፕሬዝዳንቷ ካማላ ሃሪስ ታሸንፋለች ብሏል።
ሊችማን በተጠባቂው ምርጫ ሃሪስ እንደምታሸንፍ ሲገልጽ በሙሉ መተማመን ነው ብሏል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው።
የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ግምት ባለፉት ወራት ሲወጡ ከነበሩ የህዝብ አስተያየት (ፖል) እና ትንተናዎች የተለየ ቢመስልም ከዚህ ቀደም የነበረው ሪከርድ ግን ግምቱ ለእውነት ሊቃረብ እንደሚችል ነው የተገለጸው።
ምክንያቱ ደግሞ ሊችማን ከ1984 ጀምሮ በተደረጉ 10 ምርጫዎች የገመተው ከአንዱ በስተቀር ስኬታማ መሆኑ ነው።
ከህዝብ ለሚሰበሰቡ ድምጾች ትኩረት የማይሰጠው ሊችማን በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው አሸናፊ ይሆናል ብሎ የሚገምተው በ13 መሰረታዊ መመዘኛዎች መሆኑን ይገልጻል።
በአጋማሽ ዘመን ምርጫ ውጤታማ መሆን፣ የባይደን ከምርጫ ፉክክር መውጣት እና የካማላ ሃሪስ ግርማሞገስ ማነስ ለትራምፕ አዎንታዊ ነጥብ ማሰጠቱን ተመራማሪው ተናግሯል።
ይሁን እንጂ ሃሪስ በማጭበርበር ወንጀል ስማቸው ጎልቶ አለመነሳቱና በአየርንብረት ለውጥ እና መሰረተ ልማት ዙሪያ ግዙፍ የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ያጡትን ነጥብ አንስቶላቸዋል ነው የሚሉት።
የባይደን አስተዳደር ከምርጫው በፊት በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚደርስ ይታመናል የሚለው የምርጫ ገማቹ ተመራማሪ፥ ለሃሪስ እንደ ትልቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተቆጥሮ በምርጫ ለድል እንደሚያበቃትም ይጠቅሳል።
የታሪክ ተመራማሪው “13 መስፈርቶች” አሻሚ ናቸው የሚሉ ተቺዎች ግን ምንም እንኳን ባለፉት 40 አመታት ቢሳካለትም በዚህኛው ምርጫ ሃሪስ የማሸነፍ እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን ይገልጻሉ።
ሊችማን የምርጫ ግምቱ የተሳሳተው በ2000 ነበር፤ ያልገመታቸው ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ሲያሸንፉ።
የታሪክ መምህሩ ግን ምርጫው ከህግ አንጻር የተወሳሰበና በፍርድቤት ውሳኔ የተጥናቀቀ መሆኑን በመጥቀስ ግምቱ ያልተሳካበትን ምክንያት ለማብራራት ሲሞክር መቆየቱን ፍራንስ 24 አስታውሷል።